በባሌ ዞን አርሶ አደሮች የአጭዶ መውቂያ መሳሪያ እጥረት አጋጥሟቸዋል

1262

ጎባ ታህሳስ 9/2011 በመኽሩ ወቅት ያለሙት ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበለሽ አስቀድመው ለመሰብሰብ የሚያግዛቸው የአጭዶ መውቂያ መሳሪያ/ ኮምባይነር / እጥረት እንዳገጠማቸው በባሌ ዞን ጋሰራና አጋርፋ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

ችግሩን  ለመፍታት ግብረ ኃይል አቋቁሙ እየሰራ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡

የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተጠቅመው ያለሙትን ሰብል ወቅቱን ባልጠበቃ ዝናብ እንዳይጎዳ አስቀድሞ  ለመሰብሰብ የሚያስችላቸውን ኮምባይነር ለማግኘት መቸገራቸውን አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የጋሰራ ወረዳ አርሶ አደር ከተማ በቀለ እንዳሉት በመኸሩ ወቅት በሁለት ሄክታር ማሳቸው ላይ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ስንዴ አልምተዋል፡፡

ያለሙት የስንዴ ምርት የመጨጃ ጊዜው ከደረሰ አስራ አምስት ቀናት ያለፈው ቢሆንም በኮምባይነር እጥረት የተነሳ በወቅቱ ለመሰብሰብ አለመቻለቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላው የወረዳው አርሶ አደር በከር ሱልጣን በበኩላቸው ከኮምባይነር እጥረት የተነሳ አምና በ45ብር ሂሳብ የኪራይ ዋጋ የሰበሰቡት ኩንታሉን ምርት በአሁኑ ወቅት ደላሎች እስከ 80 ብር እያስከፈሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

“የለፋንበትን ምርት አለአግባብ በደላሎች  እየተነጠቅን በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታው አካላል አስቸኳይ እልባት እንዲሰጠን እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡

የሰብል ልማቱ በወቅቱ ካልተሰበሰበ ወቅቱን ባልጠበቃ ዝናብና ለብክነትም ይጋለጣል የሚል ስጋት እንዳሳደረባቸው የተናገሩት ደግሞ በአጋርፋ  ወረዳ የአሚኛ ቀበሌ አርሶ አደር ሀጂ ሀሰን መሐመድ  ናቸው፡፡

ችግራቸው የኮምባይነር እጥረት መሆኑን ጠቅሰው የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እልባት እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብሬ ኡርጌሶ ሰለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ አርሶ አደሩ ከምርት ስብሰባ ጋር ተያይዞ ያነሱት ቅሬታ አግባቢነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ከአጎራባች  ዞኖች ከሚገኙ የኮምባይነር ባለንብረቶች ጋር በመነጋገር ምርት ወደ ደረሰበት አካባቢ በማምጣት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ አርሶ አደሩ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሳባቸውን የደላሎችን ተጽዕኖና የተጋነና የዋጋ ተመንን በተመለከተ ከኮምባይነር ባለንብረቶች ጋር የአርሶ አደሩን የመክፈል አቅም ባገነዘበ መልኩ የውል ስምምነት እየተፈራረሙ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

የምርት አሰባሰቡ ስራ በዞኑ ስምንት ወረዳዎች  መጀመሩን ያስራዱት ኃላፊው የአርሶ አደሩ ምርት ሳይባክን በወቅቱ እንዲሰበሰብና በሂደቱም በደላሎች እንዳይታለል በዞን ደረጃ  ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

እሳቸው አንዳሉት በእስካሁኑ እንቅስቃሴም በዞኑ ስምንት ወረዳዎች ውስጥ 5ሺህ ሄክታር ላይ የሚገኘው የደረሳ ሰብል 12 ኮምባይነሮችን በመጠቀም ተሰብስቧል፡፡

ቀሪውንም  እንደየወረዳዎቹ የስነምህዳር ሁኔታ በመለየት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአካባቢው  እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ የሚታየው የዳመና ክስተት ቢኖርም በሰብል ስብሰባ ላይ ተዕጽእኖ ስለሌለው አርሶ አደሩ ተረጋግቶ ምርቱን መሰብሰብ እንደለበት  ምልዕክታቸውን ያስተላለፉት ደግሞ በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ  ኤጀንሲ የደቡብ ኦሮሚያ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል የትንበያ ባለሙያ አቶ ደጀን ተረፈ ናቸው፡፡

በባሌ ዞን በ2010 /2011 የምርት ወቅት በልዩ ልዩ የሰብል ዘር ከለማው 382ሺህ ሄክታር መሬት 11 ሚሊዮን 500 ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡