የቡሬ አጋምሳ የአስፓልት መንገድ ግንባታ መቋረጥ ለችግር ዳርጎናል– የአካባቢው ነዋሪዎች

1649

ባህርዳር ታህሳስ 9/2011 በምዕራብ ጎጃም ዞን ከቡሬ አጋምሳ ያለው የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት  ግንባታ በመቋረጡ ለችግር መጋለጣቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን  የመንገዱ ስራ የዘገየው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ቢሆንም  ግንባታው የሚቀጥልበት ሁኔታ እንደሚመቻች  ገልጿል፡፡

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል በንግድ ስራ የሚተዳደሩት አቶ በላይ ዘላለም ለኢዜአ እንዳሉት  የጠጠር መንገዱ ወደ አስፓልት ደረጃ እንዲያድግ የረጅም ጊዜ ጥያቄያቸው ነበር።

መንገዱ የአማራ ክልልን ከኦሮሚያ በማገናኘት የተሻለ የንግድ ትስስር ለመፍጠርና የግብርና ምርቶችን ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው ቢጠብቁም የግንባታው መቋረጥ ተወዳዳሪ እንዳላደረጋቸው ጠቅሰዋል።

ጊዜያዊ ጥገና እንኳን የማይደረግለት በመሆኑ ተሽከርካሪዎች ሲያልፉ በሚነሳው አቧራ ለጤና ችግር እንዳላጋለጣቸው በመጥቀስ የሚመለከተው አካል ስራው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ  ትኩረት መስጠት እንዳለበት አመልክተዋል።

አቶ አበበ አየነው የተባሉት የአከባቢው ነዋሪና የህዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪ በበኩላቸው” ከቁጭ እስከ ቡሬ ያለው መንገድ በጥገና ማጣት  የተቆራረጠ በመሆኑ ተቸግረናል “ብለዋል።

የመንገዱ ሁኔታ ቀደም ሲል ከነበረው አሁን ላይ የባሰ መበላሸቱን ጠቁመው በዚህም ምክንያት በተደጋጋሚ የተሽከርካሪ እቃ እየሰበረባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

መንገዱ በመበላሸቱ በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በተገቢው ስለማይደረስ እየተጉላላ መሆኑና እሳቸውም እየሰሩ ያሉት ተቸግረውም ቢሆን  ህብረተሰቡን ለማገልገል እንጂ እንደማያዋጣቸው አስረድተዋል።

“የረጅም ጊዜ ጥያቄያችን ተፈታልን ብለን ሰርተን ለመለወጥና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማደግ ተስፋ አድርገን ነበር” ያሉት ደግሞ  አቶ ምንባለ አዝመራው ናቸው።

ነገር ግን መንገዱ በሁለት ዓመት ቆይታው አንድም የስራ እንቅስቃሴ ሳያሳይ አሁን ላይ ይባስ ብሎ በመቋረጡ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡

የመንገዱ አለመስተካከልም የትራንስፖርት ተጠቀሚውን ህዝብ ከታሪፍ በላይ እንዲከፍል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ በባሰ ሁኔታም መንገዱ ባለመጠገኑ ለእንግልት መደረጋቸውን አስረድተዋል።

ተሽከርካሪዎች ሲመላለሱ በሚነሳው አቧራም ለበሽታ እያጋለጣቸው በመሆኑ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ችግሩ እንዲፈታ እስከ ክልል ድረስ ኮሚቴ አቋቁመው በመላክ ቢሳውቁም ለሀዝቡ ቅሬታ ትኩረት ሰጥቶ የመጣ አካልና መፍትሄ የሚሰጥ አለመኖሩን ጠቁመዋል።

በቡሬ ዙሪያ ወረዳ የህዝብ ተሳትፎ አማካሪ አቶ ጌትነት ሙሉጌታ የመንገዱ በወቅቱ ካለመሰራቱ ጋር  በተያያዘ በትራንስፖርት ፍሰቱና በአካባቢው በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

በመንገዱ መጓተትም የግብርና ግብዓት በወቅቱ ለማድረስ እክል ከመፍጠሩም በላይ ትራንስፖርት ፈላጊው ህዝብ አማራጭ አጥቶ  ከታሪፍ በላይ ለትራንስፖርት በመክፈል ለመጓዝ መገደዱን ገልጸዋል።

” በዚህም  ነዋሪው ህዝብ በተደጋጋሚ ችግሩ እንዲፈታ ቅሬታ እያቀረበና ለወረዳውም የመልካም አስተዳደር መንስኤ ሆኖብናል “ብለዋል።

በተለይም ችግሩ የመንገዱ ግንባታ የፌደራል ፕሮጀክት በመሆኑና በወረዳው አቅም የማይፈታ በመሆኑ መፍትሄ ለመስጠት አለመቻሉን ጠቅሰዋል።

የመንገዱን መጓተትና መቋረጡን ለክልልም ሆነ ለፌደራል መንግስት በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም  መፍትሄማግኘት እንዳልተቻለ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ስለጉዳዩ  ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የመንገዱ ግንባታ የተጓተተው መስመሩ በሚያልፍበት አካባቢ  የነበሩ ቤቶችና ንብረቶች ለማንሳት በወሰደው ጊዜ እንዲሁም ባለፉት ሁለት ዓመታት ባጋጠመው የጸጥታ ችግርና በተቋራጩ የአቅም ማነስ  ጭምር  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በመስተካካሉ የህንድና የስፔን ጥምር የሆነው ተቋራጩ ድርጅት ወደ ስራ መግባት እንደሚጠበቅበትና ካልሆነ ለሌላ ተቋረጭ በማስተላለፍ ግንባታው  የሚቀጥልበት ሁኔታ እንደሚመቻች ገልጸዋል፡፡

አቶ ሳምሶን እንዳመለከቱት የመንገዱ ግንባታ  እንደ አውሮፓ አቆጣጣር በ2016 የተጀመረው  የነቀምቴ ቡሬ  257 ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት አካል ሲሆን በስምንት ዓመታት ለማጠናቀቅና አጠቃላይ በጀቱም ስድስት ቢሊዮን ብር ገደማ ነው፡

ከቡሬ አጋምሳ  የሚሸፍነው መንገድ 84 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ የስራ ተቋራጩን ለማነጋገር  ቢፈለግም  ከአካባቢው በመንቀሳቀሱ አድራሻውን ማግኘት አልተቻለም።