በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ላይ የሚሰራ ዓለም አቀፍ አማካሪ ምክር ቤት ተቋቋመ

56
አዲስ አበባ  ታህሳስ 9/2011  በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ላይ የሚሰራ ዓለም አቀፍ አማካሪ ምክር ቤት ተቋቋመ። ከመንግስት ጋር በጋራ የሚሰራው አማካሪ ምክር ቤቱ ከዓለም አቀፍና አገር ውስጥ የተውጣጡ ከፍተኛ ተመራማሪዎችንና ሳይንቲስቶችን ጨምሮ 134 ምሁራንን በአባልነት ይዟል። ምክር ቤቱን ያቋቋመው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ የምስረታ ጉባዔ አካሂዷል። በጉባኤው ላይ ሚኒስትር ዲኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የምክር ቤቱን አመሰራረት አስመልክቶ ጽሁፍ አቅርበዋል። በፅሁፋቸው እንዳሉትም የምክር ቤቱ መቋቋም መንግስት በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ያለውን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የጀመረውን ጥረት በብቃት ለመወጣት ያግዛል። ለዚህም ከውጭ እና ከአገር ቤት የተውጣጡ ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎችና የተለያዩ ተቋማት መሪዎች አካላት በአማካሪ ምክር ቤቱ ውስጥ እንዲካተቱ መደረጉን ገልፀዋል። ከአባላቱ መካከል 33 የሚሆኑት ከውጭ አገራት ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተመረጡ ምሁራን ናቸው።   የምክር ቤቱ አባላት ዘርፉ የሚመራበትን ስትራቴጅክ እቅድና ተቋማዊ እሴት ይገነባሉ፤ ዘርፉን ለማጠናከር ይቻል ዘንድም በአለም አቀፍ ደረጃ ኃብት የሚሰበሰብበትንና የትብብር ግንኙነት የሚፈጠርበትን መንገድ ይዘይዳሉ።   የአማካሪ ምክር ቤቱ ተጠሪነት ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይሆናል፤ የምክር ቤቱን የእለት ተለት ተግባር በቅርበት የሚመራ  ሴክረቴሪያትም ይቋቋማል።   የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አመራር ክህሎት ችግሮች በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።   ዘርፉን ከኢንዱስትሪው ጋር የማስተሳሰር ጉዳይም ትልቅ ድክመት እንዳለበት ሚኒስትሯ ገልፀዋል።   "ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ደግሞ ከቀድሞ አካሄድ በመውጣት በአዲሰ መልክ መስራትን ይጠይቃል፤" ሲሉም አመልክተዋል። በመሆኑም የአገሪቱን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የልህቀት ማዕከል የማድረጉ ጉዳይ "ከቃላት በላይ በተግባር መለወጥ አገሪቱ አሁን በአጣዳፊ ሁኔታ የምትሻውና ለነገ የማይባል ስራ ነው" ብለዋል። አገሪቱ ይህን ማድረግ የሚችሉ በቂ ምሁራን ከውስጥም ከአገር ውጭም እንዳሏት በመጥቀስ ከዚህ በፊት ግን ''ሁሉ ነገር በፖሊቲካ ዓይን እየታየ እነዚህ የአገር ልጆች የድርሻቸውን የሚወጡበት ምቹ ሁኔታ ሳይፈጠር ቆይቷል'' ሲሉም አብራርተዋል። አሁን ግን ይህን የሰው ሃይል በአግባቡ በመጠቀም ከችግሮቹ መላቀቅ እንደሚቻልም ተናግረዋል። በመሆኑም የምክር ቤቱ አባል እንዲሆኑ የተመረጡ ምሁራን ያልተቆጠበ ድጋፋቸውን በማበርከት የተሻለች አገር መገንባት የሚችል ትውልድ ማፍራት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱም ጥሪ አቅርበዋል። በመድረኩ የተሳተፉ ምሁራን በበኩላቸው ምክር ቤት ለማቋቋም የቀረበውን ሀሳብ አድንቀዋል። ወደፊትም ባለቸው ሙያና ልምድ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል። በመድረኩ ያልተገኙ ውጭ አገር የሚኖሩ አባላቶችም አገራቸውን እንዲያገለግሉ የተደረገላቸውን ግብዣ በደስታ አንደተቀበሉም ታውቋል። በአማካሪ ምክር ቤቱ የተሰየሙት ምሁራንና ሌሎች አካላት ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት በአማካሪነት ያገለግላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም