የመንግስታቱ ድርጅት የደቡብ ሱዳንን የሶስት ዓመት የልማት መርሃ ግብር ይፋ አደረገ

69
አዲስ አበባ ታህሳስ 9/2011 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳንን የሶስት ዓመት የልማት ትብብር መርሃ ግብር ይፋ አደረገ። መርሃ ግብሩ የድርጅቱ የተለያዩ ኤጀንሲዎች በደቡብ ሱዳን የሚያካሄዷቸውን የልማት እንቅስቃሴዎችን ለመምራት የሚያግዘው መሆኑን የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች መግለፃቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል። ከመጪው የአውሮፓ ዓመት ጀምሮ ለሶስት ዓመታት የሚቆየው መርሃ ግብሩ ትናንት ይፋ የተደረገው በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችሉ አዳዲስ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እየታዩ በመጡበት  ወቅት መሆኑን በደቡብ ሱዳን የድርጅቱ ልዩ መልዕክተኛ አለን ኖውዴሁ ተናግረዋል። በመርሃ ግብሩ መሰረት ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል የሰላም ግንባታ፣ መንግስታዊ አስተዳደርን ማጠናከር፣  የምግብ ዋስትና ሁኔታን ማሻሻል፣ የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት አንዲንሰራራ ማገዝ፣ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣ ሴቶችንና ወጣቶችን ማብቃት ይገኙበታል። የመንግስታቱ ድርጅት የልማት መርሃ ግብር ውጤታማ ይሆን ዘንድ በደቡብ ሱዳን የሚካሄደው የሰላም ግንባታ ሂደት መጠናከር እንዳለበት ነው ልዩ መልዕክተኛው ያሳሰቡት። የአገሪቱ መንግስትም አዲስ በቀየሰው ብሄራዊ የልማት ስትራቴጂው ቁልፍ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ መመደብ እንዳለበትም አስገንዝበዋል። የደቡብ ሱዳን የገንዘብና ኢኮኖሚ ፕላን ምክትል ሚኒስትር ጎች ማኩች ማዮል በበኩላቸው አገራቸው አዲስ ብሄራዊ የልማት ስትራቴጂ ቀይሶ በቅርቡ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሰው ይህንን የተመድ መርሃ ግብር ከብሄራዊ እቅዱ ጋር በማቀናጀት ለመተግበር የሚያስችል ስልት እንደሚቀየስ ተናግረዋል። በደቡብ ሱዳን የሚካሄደው የርስ በርስ ጦርነት አያሌዎችን ለሞት፣ ለመፈናቀልና ለስደት ዳርጓል። አገሪቱንና ህዝቧን መልሶ ለማቋቋም በመጪው የአውሮፓ ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የአገሪቱ መንግስት በቅርቡ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም