ምክር ቤቱ ብሄራዊ የሃዘን ቀን አወጀ

70
አዲስ አበባ ታህሳስ 8/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየትን አስመልክቶ ነገ ብሄራዊ የሃዘን ቀን ሆኖ እንዲውል አውጇል። ህልፈታቸውን ተከትሎ ቅዳሜ ታህሳስ 6 ቀን 2011 የተቋቋመው የቀብር ሥነ ስርዓት አስተባባሪ ብሄራዊ ኮሚቴም የድርጊት መርሃ ግብሮችን ይፋ አድርጓል። በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች አዋጅ ቁጥር 653/2001 እና በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 ላይ በተደነገገው መሰረት ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ብሄራዊ የሀዘን ቀን ሆኖ ይውላል። በዚህም መሰረት በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በአገሪቷ መርከቦች፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ለአንድ ቀን የአገሪቷ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል። የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን ህልፈትን ተከትሎ ቅዳሜ ታህሳስ 6 ቀን 2011 የቀብር ሥነ ስርዓት አስተባባሪ ብሄራዊ ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል። ኮሚቴው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ከገንዘብ ሚኒስቴር፤ ከመከላከያ ሚኒስቴርና ከፌዴራል ፖሊስ የተውጣጡ አባላት አሉት። አስተባባሪ ብሄራዊ ኮሚቴው ትናንት ባደረገው ስብሰባ መሰረት የሽኝትና የቀብር ሥነ ስርዓቱን  ለማከናወን መርሃ ግብር አውጥቶ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል። ከታህሳስ 8 እስከ ታህሳስ 9 ቀን 2011 እስከምሽቱ 12 ሰዓት ጦር ሃይሎች ሆላንድ ኤምባሲ ፊት ለፊት በሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው ከፍተኛ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት፤ የፌደራልና የክልል አፈ-ጉባኤዎች፤ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፤ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የውጭ አገር አምባሳደሮች በተዘጋጀው የሃዘን መግለጫ መዝገብ ላይ መልእክቶቻቸውን ያሰፍራሉ። የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና የቆንስላ ጽሀፈት ቤቶችም በተመሳሳይ የሃዘን መግለጫ መዝገቦችን አዘጋጅተዋል። ማክሰኞ ታህሳስ 9 ቀን 2011 ከምሽቱ በ12 ሰዓት አስከሬናቸው ከጦር ሃይሎች ሆስፒታል ወደ መኖሪያ ቤታቸው ተወስዶ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ቤተሰቦቻቸው አቀባበል ይደረግለታል። ረቡዕ ታህሳስ 10 ቀን 2011 ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ሕዝባዊ ስንብት በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድም አስተባባሪ ብሄራዊ ኮሚቴው አስታውቋል። በመጨረሻም ከስንብት በኋላ ቤተሰቦቻቸውና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀብር ሥነ ስርዓታቸው ይፈፀማል። በ95 ዓመታቸው ሕይወታቸው ያለፈው የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ለአገራዊ አገልግሎታቸው የሚመጥን ሽኝት እንደሚደረግላቸውና ለክብራቸው መድፍ እንደሚተኮስ ኮሚቴው ገልጿል። የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በህይወት ዘመናቸው ከወታደርነት እስከ ርዕሰ ብሄር በመድረስ አገራቸውንና ህዝባቸውን አገልግለዋል። ኢትዮጵያን ለ12 ዓመታት በርዕሰ ብሄርነት አገልግለው የስራ ዘመናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በአረንጓዴ ልማት፣ በአይን ብሌን ልገሳ ማህበር እና በሌሎች የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም