ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ድንበር ዘለል የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል ተሰማሙ

82
ታህሳስ 9/2011 የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ድንበር ዘለል  የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመከላከል ተሰማምተዋል። ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትላት በአቡዳቢ ባደረጉት ውይይት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የደረሰበትን ደረጃ አንስተው በመነጋገር ወዳጅነታቸውን የበለጠ በማጠናከርና  አገሮቹን ተጠቃሚ ለማድረግ መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚቴስትር ቃል አቀባይ የላከው መግለጫ ያመለክታል፡፡ በአገር ውስጥ የተጀመረውን የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጥረት ለመደገፍ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢኮኖሚ ላይ የሚፈፀምን ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከልና ሲፈፀሙም ተቀናጅቶ ለመመርመር በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በተሳተፉበት በዚህ ውይይት በኢንቨስትመንት፣ በግዥ እና ሌሎች ተዛማጅ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል እና ለመዋጋት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ከመግባባት ደርሰዋል፡፡ በቀጣይ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከል የሚካሄድ ጠንከራ ጥረትን በህግ ማዕቀፍ ለማስደገፍና አብረው ለመስራት መስማማታቸው ተገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም