ችሎቱ በእነረዳት ሳጂን ኪዳኔ አሰፋና በእነትግስት ታደሰ መዝገብ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

57
አዲስ አበባ ታህሳስ 8/2011 ችሎቱ በእነ ረዳት ሳጂን ኪዳኔ አሰፋ እና በእነ ትግስት ታደሰ መዝገብ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ከ7 አስከ 14 ቀናት የሚደርስ  ተጨማሪ  የምርመራ ጊዜ ፈቀደ። የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት በዛሬው ውሎው የተለያዩ የሙስናና ሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ተመልክቷል። በሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች ረዳት ሳጂን ኪዳኔ አሰፋና አቶ ሳሙኤል ግዲሳ ላይ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀናት ፈቅዷል። ቀጠሮው ከታህሳስ 5 ቀን ጀምሮ የሚታሰብ ሲሆን ለታህሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል። በሌላ በኩል ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ አላግባብ የጥቅም ትስስር በማድረግ የሙስና ወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል ተብለው በቁጥጥር ስር የሚገኙት ትእግስት ታደሰ፣ ጋዜጠኛ ፍጹም የሺጥላ እና አቶ ቸርነት ዳና ጉዳይንም ተመልክቷል። በዚህም በትግስት ታደሰና በአቶ ቸርነት ዳና ላይ ከታህሳስ 5 ጀምሮ የሚታሰብ የ10 ቀናት ሲፈቅድ፣ በጋዜጣኛ ፍጹም የሺጥላ ላይ ደግሞ የ7 ቀናት የተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። በዚህም ተጠርጣሪዎቹ እንደቅድም ተከተላቸው ለታህሳስ 12 እና 15 ቀን 2011 ዓ.ም ችሎት ይቀርባሉ። በሌላ በኩል በዕለቱ ችሎት የቀረቡት የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች ተስፋዬ ዑርጌ፣ ማዕሾ ኪዳኔ፣ ሃዱሽ ካሳ፣ እንዲሁም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የህብረት ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሻለቃ መስፈን ስዩም ጉዳይ ለነገ በአዳር ተቀጥሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም