የኢትዮጵያ የሰላም እናቶች "የሰላምን ነገር አደራ" ሲሉ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን አሳስበዋል

112
አዲስ አበባ ታህሳስ 8/2011 በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በመዘዋወር ስለ ሰላም በመምከር ላይ የሚገኙት "የሰላም እናቶች" ዛሬ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተዋል። የሰላም እናቶቹ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ያደረጉትን ጉዞ በማጠናቀቅ ዛሬ የመጨረሻ መዳረሻ በሆነችው አዲስ አበባ በመገኘት ''የሰላምን ነገር አደራ'' ብለዋል። የሰላም እናቶቹ ቡድን አባላት ላለፉት 25 ቀናት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ስለሰላም ሰብከዋል፤ መክረዋል። ቡድኑ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 21 እናቶችን ያቀፈ ነው። ከየክልሎቹና የከተማ አስተዳደር መሪዎች ጋር ተወያይቷል፤ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማምራትም ከተማሪዎች ጋር ስለሰላም መክሯል። እናቶቹ በቆይታቸው በየደረሱበት ሁሉ የሰላም መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ፣ የአገር ሽማግሌዎችና ተማሪዎች ፊት ተንበርክከው "ሰላም አውርዱ" እያሉም ተማፅነዋል። ዛሬ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተገናኙበት ወቅትም አስተዳደሩ ታች ድረስ ወርዶ ህዝቡን ስለሰላም እንዲያወያይ የሰላም እናቶቹ አደራ ብለዋል። ትውልዱም ሰላምን በማስቀደም የድርሻቸውን እንዲወጣ፤ እናቶች ደግሞ ሰላምን ለማውረድ ቀድመው እንዲሰለፉም ተማጽነዋል። በከተማ አስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበረዊ ዘርፍ አስተባባሪና የኮሙኑኬሽን ቢሮ ኃላፊው ኢንጅነር እንግዳ አወቀ አደራቸውን ተቀብለዋል፤ ተግባራዊ ለማድረግም ቃል ገብተዋል። የሰላም እናቶቹ ላለፉት ቀናት ያከናወኑት ተግባር ትውልዱ ስለሰላም ተገቢ የሆነ ግንዛቤ እንዲያገኝ ከማስቻል አኳያ አርዓያ የሚሆን እንደሆነ እንጂነር እንግዳ ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም