ሕብረ -ብሄራዊ ስርዓት ለአንድነት…

1069
ሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ) ፌደራሊዝም የሚለው ቃል “ ፊውደስ” ከሚለው የላቲን ቃል የተወሰደ መሆኑን መጽሃፍት ይነግሩናል። ትርጉሙም ቃል-ኪዳን፣ ኮንትራት፣ ድርድር ወይም የአብሮነነትና በጋራ የመኖር ውልን ይወክላል። ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውልም በሰው ልጅና በፈጣሪ  መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ለመግለጽ ነበር።  በጥንታዊ ዘመን በተለያዩ ጥቃቅን ግዛቶች የሚኖቱ ማህበረሰቦች እራሳቸውን ከወረራና ከልዩ ልዩ አደጋዎች ለመጠበቅ ሲሉ ውስጣዊ ማንነታቸውንና አካባቢያዊ ግዛቶቻቸውን እንዲጠብቁ የጋራ አስተዳደርና ህብረት ለመፍጠር ይስማሙ ነበር። ይህንን ፈቃደኝነት የመሰረቱትን ህብረት የሚገልጽ ቃል በሚፈልጉበት ጊዜም ፌደራል ወይም ፌደራሊዝም የሚል ቃል ተስማሚ ሆኖ አገኙት። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቃሉ የፖለቲካ ትርጉምና ይዘት እየወረሰ በመምጣት እኤአ በ1291 የተመሰረተው የስዊስ ኮን-ፌዴራላዊ ስርዓትና ከዚያ ቀጥሎ የተመሰረቱ ፌዴራላዊ ስርዓቶች ህብረታቸውንና የመንግስታቸውን ቅርጽ ለመግለጽ ቃሉን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ስለሆነም ፌዴራላዊ የመንግስት  አወቃቀር ማለት የራስ አስተዳደርና የጋራ አስተዳደርን ያጣመረ፤ የሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ መንግስታት የሚፈጥሩት በቃል ኪዳን የሚመሰረትና የሚመራ አጋርነት ነው። አጋርነቱ በመካከላቸው ሊኖር የሚገባውን የስልጣን ክፍፍልና ዝምድና ይወስናል፤ አንዱ የሌላውን ቅንነትና አብሮነት እሳቤ ተቀብሎ በማመን ላይ ይመሰረታል። እንዲሁም አንዱ የሌላውን ልዩ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት የመሳሰሉትን መገለጫዎች  በማክበር በእኩልነት ይጠብቃል። የፌደራሊዝም ስርዓት በዓለም አገራት ያለው ተሞክሮ ከዓለም ህዝብ መካከል 40 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የሚኖርባቸው 28 የዓለማችን አገራት የፌደራሊዝም ስርዓትን ይከተላሉ፤ ወይም ፌደራላዊ ተብለው ተፈርጀዋል። እነዚህ ሀገራት እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሰፊ ግዛት ያላቸው መሆናቸውና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መከተላቸው ፌደራሊዝም ከነጻነትና ከዴሞክራሲያዊ መረጋጋት ጋር ሊጣመር ችሏል። በተባበሩት መንግስታት ስር ተመዝግበው ካሉ 192 ሀገራት መካከል 28ቱ ፌደራላዊ ስርዓትን የሚከተሉ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታል። ብዙዎቹ እንደሚያስቡት ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ ብቻ ያለ አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን የሚያሰፋ ስርዓት አይደለም። ስርዓቱ ይህንን የማድረግ ዕድሉ እጅግ አናሳ ነው። ፌደራሊዝም ሀገርን የሚበታትንና አንድነትን የሚያጠፋ ቢሆን ኖሮ ከኢትዮጵያ በፊት ፌደራሊዝምን ቀድመው የጀመሩት ሀገራት ህልውና እስከ ዛሬ አክትሞ ነበር። እውነታው ግን ፌደራሊዝም ብዝሃነትን በአንድ ላይ አጣምሮ የሚይዝ ስርዓት ነው። እነ አሜሪካና ስዊዘርላንድ ፌዴራላዊ ስርዓትን ተቀብለው መተግበር ከጀመሩ ምዕተ አመት አስቆጥረዋል። እንደተባለው ስርዓቱ ሀገርን አደጋ ውስጥ የሚጥልና አንድነትን የሚያጠፋ ቢሆን ኖሮ ዛሬ አሜሪካም ሆነ ስዊዘርላንድ የሚባሉ አገራትን ላናይ እንችል ነበር። አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1789 በህገመንግስት የተረጋገጠ ፌደራላዊ ስርዓትን በሀገሯ ላይ እውን አድርጋለች። ስዊዘርላንድ ደግሞ እ.ኤ.አ በ1848 ስርዓቱን በህገመንግስቷ እውቅና አሰጥታ ዘርግታለች። ጀርመንም እ.ኤ.አ.በ1871 ፌደራላዊ መንግስትን ይፋ አድርጋለች። በመቀጠልም ካናዳ፣ ቤልጂየም፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ አርጄንቲና፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የተለያዩ ግዛቶች፣ ቼኮስሎቫኪያ፣ ከኮሚኒዝም መፈራረስ በኋላ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ወደ ፌዴራል ስርዓት በሂደት እንደተቀላቀሉ የዘርፉ አዋቂዎች ከጻፏቸው ሰነዶች መረዳት ይቻላል። የኢትዮጵያ ሕብረ-ብሄራዊ ፌደራል ስርዓት መነሻዎች የማንነት (የብሄር፣ብሄረሰብ፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ታሪክ…) ጭቆና ፣ የመልማት መብት መነፈግ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዓፈና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ናቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ሀገራችን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርዓትን ላለፉት 27 ዓመታት  ተግብራዋለች፡፡ በዚህም  በርካታ ስኬቶችን ያጣጣመች ሲሆን፣ የአገሪቱ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ስርዓቱ የብሄር፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የቋንቋ፣ የኃይማኖት፣ የጾታ ብሎም የባህል ብዝሃነት ጥያቄዎችን በብቃት ለማስተናገድ የተቀረጸ እንደመሆኑ ጥያቄዎቹም በልማት፣ በሠላም እና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው እውን መሆን ምላሽ እያገኙ መጥተዋል፡፡ አገሪቷ አሁን እየተከተለች ባለችው የፌደራል ስርዓት ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋቸውን መጠቀም፣ ማሳደግ እንዲሁም ባህላቸውን የማዳበርና የማስፋፋት፣ ታሪካቸውንም የመንከባከብ መብት ያላቸው በመሆኑ ከሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ጋር በመሆን ኢትዮጵያዊነትን በመገንባት በኩል እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት ስላላቸው ለኢትዮጵያ አንድነት እውን መሆን አያቅማሙም፡፡ የፌደራል ስርዓቱ ኢትዮጵያዊነትን በመገንባት በኩል ያለውን ሚና አስመልክቶ በፌደሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህገ መንግሥት ተርጓሚና ….ዳይሬክተር አቶ ሙልዬ ወለላው፣ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያውያን የተለያየ ብሄር፣ ቋንቋ፣ ባህል እምነት እንዲሁም ስነ ልቦና ያላቸው ቢሆኑም፣ እነዚህን በመያዝ ለረጅም ዘመናት በአብሮነት የኖሩ ህዝቦች በመሆናቸው ኢትዮጵያዊነታቸውን ሳይዘነጉት እዚህ ደርሰዋል፤ በአሁኑ ወቅትም ይህንኑ ማስቀጠል አስቸጋሪ አይሆንባቸውም፡፡ ‹‹ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ብዝሃነት አለን፤ ይህን ብዝሃነት ማስተናገድ የምንችለው በፌዴራል ስርዓት ውስጥ ነው፡፡ ትልቁ ነገር ግን እዚህ ላይ የሚነሱ ክርክሮች መኖራቸው ነው፡፡ አሁንም ድረስ ስርዓቱን በተመለከተ በየመድረኩም በተለያዩ ጎራዎች በመከፋፈል የሚከራከሩ እንዳሉ ይታወቃል›› ይላሉ፡፡ ‹‹በገዥውም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልግ ጥርጥር የለውም››የሚሉት አቶ ሙልዬ፣ ልዩነቱ ያለው ምን አይነት ፌዴራሊዝም የሚለው ላይ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶቹ የመልከዓ ምድር አቀማመጥንና ክልልን ለልማትና ለኢኮኖሚ እድገት አመቺ ነውና አካባቢያዊ የሆነ ፌዴራሊዝም ያስፈልጋል እንደሚሉም ይጠቁማሉ፡፡ እንደ አቶ ሙልዬ ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት አካባቢንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በኩል የሚቆሙት ደግሞ ስርዓቱ የተመሰረተው በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሆኖ ቢሆን በብሄር ብሄረሰቦች መካከል መከፋፈል አይኖርም ነበር ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች በዘር፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት ሳይከፋፈሉም በመግባባትና በፍቅር መዝለቅ ይችላል የሚል አስተያየት ያቀርባሉ፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፣ የተባሉት ለውጦች ይመዝገቡ እንጂ ስርዓቱ በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ አለመሆኑ ግልጽ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ስርዓቱን ተግባራዊ የሚያደርጉት የአመራር አባላት የሚፈጽሙት ስህተት ነው፡፡ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 ላይ ሁለት ንዑስ አንቀጾች ያሉ ሲሆን፣ አንደኛው የመዘዋወር ነጻነትን የሚደነግግ ነው፤ በዚህም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በህጋዊ መንገድ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኘ የውጭ ዜጋ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገ ጊዜ ከአገር የመውጣት ነጻነት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ‹‹ስርዓቱ ምንም ችግር የለበትም፤ ለውጦችንም ማየት አስችሏል፤ ነገር ግን ምንም እንከን የለውም የምንል እና እውነታውን የምንደብቅ ከሆነ መጥፎ ነገሩን እየደመርን ነው የምንጓዘው›› የሚሉት አቶ ሙልዬ፣፡”ለምንድን ነው ሰዎች የሚፈናቀሉት” የሚለውን ማየቱ ተገቢ ነው ሲሉ እንደ አብነት ይጠቅሳሉ፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ ይዘት ለኢትዮጵያዊነት ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑ ታምኖበት መነጣጠልን ሊያመጡ የሚችሉ ክፍተቶችን ግን በመረባረብ መድፈን መቻል ዋናው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ከክፍተቶቹ አንዱ በብሄር ብሄረሰብ ስም የሚመጡ ጥላቻዎችንና ግጭቶችን ማምከን መቻል ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዶች በግለሰብ ደረጃ የተደረገን ጸብ ብሄር ከብሄር ጋር እንደተጣላ አድርገው ሲወስዱ ይስተዋላል፡፡ ይህ መቆም ይኖርበታል፡፡ ይህ አይነቱ ድርጊት  ከፌዴራል ስርዓት ጋር ተቃራኒ ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ መንግሥት አስታራቂ ዳኛ ሆኖ በመካከል አለና እሱን አውቆ መተግበር ከምንም በላይ ውጤታማ ያደርጋል፡፡ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት አግባብነትና ጥራት ዳይሬከተር ዶክተር እንዳለው ፉፋ እንደሚሉትመከባበርና መፈቃቀድ ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ከተፋለሱ ዋጋ ያስከፍላል፤ የህይወት መጥፋትም ይከሰታል፡፡ አገርም እንደ አገር እንዳይቀጥል ሊያደርግ ይችላል፡፡  ስርዓቱን  ህዝቡ በአግባቡ ይረዳ ዘንድ ሥራዎች  መሠራት ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት  ዶክተር እንዳለው፡፡ እንደ ዶክተር እንዳለው አባባል፤ ኢትዮጵያዊነትን ለመገንባት ከሌሎች አገሮች ታሪክ መማርም ይጠቅማል፡፡ የሶርያንና ሌሎች አገሮችን ተሞክሮ መውሰዱም መልካም ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ከትንሽነት አልወጡም፡፡ የአንዳንድ አገራት ጉዳይ ሲታይ ከገቡበት ግጭት ያልወጡበት ምክንያት ምን ይሆን ተብሎ ሲፈተሽ ብዝሃነትን አለማክበራቸው ምክንያት ሆኖ ይወጣል፡፡ ሌላው ደግሞ ትውልዱን መልካም የሆነውን ሁሉ ማስተማር ይጠበቃል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የምንገልጽበት ቃል በራሱ አስተማሪ መሆን አለበት፡፡ ጥሩ የሚባሉ አገሮች እኮ የኢትዮጵያውያን አይደሉም፡፡ ከፋም ለማም ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን አገር መሆኗ መዘንጋት የለበትም፡፡ ‹‹ቀደም ሲል በአገራችን እኮ ስም እስከመቀየር የተደረሰበት ወቅት መኖሩ አይካድም ፤ ወደ አሁኑ ሲመጣም ማህበረሰባችን እርስ በእርሱ ምን ያህል ተዋውቋል ብለን መጠየቅ ይኖርብናል›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ፐሮፌሰር ተሰማ ታኣ፤ ኢትዮጵያ ስትባል አገር ናት፡፡ ይህች አገር እንዴት እንደተመሰረተችና ሰዎቹ እንዴት እንደተሰባሰቡ ደግሞ ከታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ ልዩ ልዩ ብሄር፣ በሄረሰቦችና ህዝቦች አንድ ላይ የተጠቃለሉበት ጊዜ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም ይላሉ፡፡ ‹‹ይህቺ አገር ስትመሰረት ቆይታ እዚህ የደረሰችው በአንድና በሁለት ሰው ብቻ ሳይሆን በብዙሃኑ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ የመጣው ከላይ ወደታች ነው፡፡ ይህ ማለት በኃይል በጉልበትም የሚከናወን ነው ማለት ይቻላል፡፡ በጥቅሉ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አይደለም›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቀደም ባሉት ጊዜያትም የብሄረሰብ ግጭቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የማእከላዊውን መንግሥት ለማዳከም ብዙ ጊዜ ተሞክሯል፡፡ የተለያዩ ብሄረሰቦች ከውጪ ሀይሎች ጋር በማበር ማዕከላዊውን መንግሥት ለማዳከም ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ ያንን ያደረጉበት ምክንያት መብታቸው ስለተረገጠ ብቻ ነው፡፡ ሀብታቸውንም በአግባቡ ባለመጠቀማቸውም ነው፡፡ ከእነሱ ግብር ይሰበሰባል እንጂ እነሱን የጠቀመ ነገር ባለመኖሩ ማዕከላዊውን መንግሥት በጣም ይቃረኑ ነበር፡፡ ማዕከላዊው መንግሥት ደግሞ ወታደር አደራጅቶ ሁሉንም ዝም ያሰኛል፡፡ ከአንዱ ስፍራ አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ ያሰፍራል፡፡ ይህ ሁኔታ በመቀጠሉ ችግሮች በአገርና በህዝብ ላይ ያለ መቋጫ ሲቀጥሉ ነበር፡፡ ደርግም አንዳንድ ችግሮችን ሲፈታ የብሄር ብሄረሰቦችን ጥያቄ አልመለሰም ፡፡ የብሄር ብሄረሰብ ጥናት ክፍል አቋቁሟል ፡፡ የተካሄዱት ጥናቶች ግን የት እንደገቡ አይታወቅም፡፡ ግጭትን ለማስቀረትና የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በሚያስችል መልኩ አደራጃለሁ ብሎ ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው የትጥቅ ትግል ውስጥ የተገባውና ኢህአዴግም የተመሰረተው፡፡ የነበረውን ችግር ለማስቀረት የህገ መንግሥቱን መሠረት በፌደራሊዝም ላይ እንዲሆን አድርጓል፤ ፌዴራሊዝሙ የሁሉንም ጥያቄ በሚያስተናግድ መልኩ ነው  በህገ መንግሥቱ  የተደነገገው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ተሰማ ማብራሪያ፤ እያንዳንዱ ክልል ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ለራሱ የሚገባውን አድርጎ ለማዕከላዊው መንግሥት ፈሰስ ማድረግ የሚጠበቅበትን በትክክል መስጠት ሲችል ነው ፌዴራሊዝም የሚመጣው፡፡ ይህን ሲያደርጉ ግን በየክልሉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችም አሉና ክልሉን እንደራሳቸው መያዝ ይኖርባቸዋል ፡፡ ይሁንታቸውና ፈቃዳቸው መኖር አለበት፡፡ የውስጣቸውን ጸጥታ መጠበቅ መቻል አለባቸው፡፡ በራሳቸው ውስጥ ያሉትን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በልዩ ልዩ ባህል አደረጃጀት አክብረው ሲገኙ ነው ፌዴራሊዝም ግቡን የሚመታው፡፡ በመሰረቱ የኢትዮጵያን ችግር ይፈታል ተብሎ የታሰበው በትክክል ፌዴራሊዝም በስራ ሲተረጎም ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ተሰማ ገለጻ፤ የፌዴራሊዝም ስርዓት ለኢትዮጵያ መፍትሄ ነው፡፡ ስርዓቱ የእያንዳንዱን ባህል፣ ቋንቋ ጠብቆ የሚያስኬድ በመሆኑ መልካም ነው፡፡ ሰዎች በባህርያቸው እውቅና ይፈልጋሉ፡፡ ማንነታቸውም የአገር አንድነትም ሳይነካ እንዲሄድ ይፈልጋሉ፡፡ የትኛውም ህዝብ ደግሞ ማንነቱ ከተጠበቀና እውቅና ከተሰጠው ኢትዮጵያን ከተለያዩ ተጽዕኖዎች ያድናል፡፡ ማንነት ካልታወቀ ኢትዮጵያ ለእኔ ምንድን ናት ወደሚለው ያስኬደዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የምንገነባው ከስር ወደላይ ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ብሄር ብሄረሰብ የራሱ ቋንቋና ባህል ከተጠበቀለት ‹‹አገሬ ኢትዮጵያ ናት›› ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ መብቱ ካልተከበረ ደግሞ ‹‹ትቻት ነው የምወጣው ›› ሊል ይችላል ሲሉ ያብራራሉ ፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ተሰማ አገላለጽ ፤ይህ የፌዴራል ስርዓት እንደሚጠበቀው ተግባራዊ ካልተደረገ እንዳለፈው ስርዓት ማንኛውም ትዕዛዝ ከላይ ወደታች ብቻ ይወርዳል፡፡ በዚህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ መተማመን አይኖርም፡፡ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ማንም ማንንም መግዛት አይችልም፡፡ እንደገና ትግል ይከሰታል፡፡ ህግ የሁሉም የበላይ ነው፡፡ ስለዚህም በህግ ነው መንቀሳቀስ የሚጠበቀው፤ የፌዴራል ስርዓቱን በአግባቡ መተግበር ያስፈልጋል ፡፡ እንደ ምሁራኑ አገላለጽ ፤ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው ስርዓት ነው፡፡ ስርዓቱ የህዝብን መብት ያረጋገጠ ስለመሆኑም ይታመናል፡፡ ለዘመናት ጥያቄ ሆኖ የቆየውንም ችግር ፈትቷል፤ ነገር ግን በዚህ ስርዓት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አካላት ህዝብን ከለላ አድርገው የራሳቸውን ዓላማ ሲፈጽሙ ይስተዋላል፤ በዚህም ስርዓቱ በአግባቡ እንዳይተገበር ሲያደርጉም ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋልና እነዚህ ወገኖች ስርዓቱ ከሚፈቅደው ውጭ ለራሳቸው ጥቅም የሚያደርጉትን ሩጫ መግታት ይኖርባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም