የአምቦ -ወሊሶ የአስፋልት መንገድ ግንባታ በመቋረጡ ቅሬታ አስነስቷል

115
አምቦ ታህሳስ 8/2011 የአምቦ -ወሊሶ 63 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአስፋልት መንገድ ግንባታ በማያውቁት ሁኔታ በመቋረጡ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው በአምቦ አካባቢ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ከነዋሪዎች መካከል አቶ ዮሴፍ ነገሰ ለኢዜአ እንዳሉት  የአምቦ – ወሊሶ መንገድ የግንባታ  ስራው የተጀመረው  ከ3 ዓመታት በፊት ነው፡፡ "መንግስት መንገዱን ወደ አስፋልት ደረጃ ለማሳደግ ወስኖ ስራ ተጀምሮ ስናይ የዘመናት ጥያቄያችን በመመለሱ በጣም ተደስተን የነበረ ቢሆንም የመንገዱ ግንባታ ተመልሶ በመቋረጡ አዝነናል" ብለዋል፡፡ ሌላው የወረዳው አርሶ አደር አቶ ሰይፉ በቀለ በበኩላቸው ለመንገዱ ግንባታ ተብሎ ተቆፋፍሮ ለረጅም ጊዜ ሳይሰራ የቀረው መንገድ መውጪያ መግቢያ እንዳሳጣቸው ተናግረዋል፡፡ የመንገዱ ግንባታ በጅምር መቅረቱም  ምርታቸውን ወደ  ገበያ አጓጉዘው ለመሸጥ  አዳጋች እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ የሚመለከተው የመንግስት አካልም የተቋረጠው የመንገድ ግንባታ ተጀምሮ የአርሶ አደሩ ተስፋ እውን እንዲሆን እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ የመንገዱ ግንባታ በተጀመረበት ጊዜ በመደሰት ንብረታቸውን በሁለት ቀን ውስጥ ማንሳታቸውን የተናገሩት ደግሞ የአምቦ ከተማ ነዋሪ አቶ አዲሱ ግርማ ናቸው፡፡ ሆኖም ተቋራጩ በአካባቢው የቆፈረው ጉድጓድ እንስሳታቸውን መግቢያና መውጪያ ከማሳጣቱም በላይ አንድ በሬ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ እግሩ እንደተሰበረባቸው ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ስለጉዳዩ  በስልክ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ተቋራጩ  ስራውን ውል በገባበት የጊዜ ገደብ እያከናወነ አለመሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ባለሥልጣኑ የተቋጩን  ውል ለማቋረጥ በሂደት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል። "በአጭር ጊዜም ሂደቱ ተጠናቆ ለሌላ ተራጭ በመስጠት የመንገዱን ግንባታ በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን ጥያቄ እንመልሳለን" ነው ያሉት ። ለመንገዱ ግንባታ ከ1 ቢሊዮን 200 ሚሊዮን  ብር በላይ በጀት እንደተመደበለትም ተመልክቷል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ፕሮጀክቱን የሚገነባው ኤልሳሜክስ የተባለው የስፔን ተቋራጭ  ለማነጋገር  አድራሻውን ማግኘት አልተቻለም።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም