ሚኒስቴሩ የመቶ ቀናት ዕቅዱን ሊለካ በሚችል መልኩ አስተካክሎ እንዲያቀርብ ታዘዘ

91
አዲስ አበባ ታህሳስ 8/2011 የትራንስፖርት ሚኒስቴር የመቶ ቀናት ዕቅዱን ሊለካ በሚችል መልኩ አስተካክሎ እንዲያቀርብ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትዕዛዝ ሰጠ። ሚኒስቴሩ የዕቅዱ መነሻ የሆኑት በበጀት ዓመቱ ሁለተኛ ሩብ ዓመት የተያዙ ተግባራትን ለመፈፀም ማነቆ የሚሆኑ ጉዳዮችን መፍታት እንደሆነም ገልጿል። የምክር ቤቱ የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትራንስፖርት ሚኒስቴርን የመቶ ቀናት ዕቅድ ዛሬ ገምግሟል። ሚኒስቴሩ ባቀረበው የመቶ ቀናት ዕቅዱ ተግባራቱ መቼ እንደሚያከናውኑ ያስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ባለመኖሩ ዕቅዱን ሊለካ በሚችል መልኩ አስተካክሎ እንዲያቀርብ ቋሚ ኮሚቴው ትዕዛዝ ሰጥቷል። የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ስራዎች በምን ያህል ጊዜ እንደሚከናወኑ እና ለቋሚ ኮሚቴው ክትትልና ቁጥጥር በሚያመች መልኩ ዕቅዱ መከለስ እንዳለበትም አመልክቷል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ የሚያከናውናቸውን ዋና ዋና ተግባራት ለይቶ መቶ ቀናት ከመጠናቀቁ በፊት ተገባራቱን በጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጥ አለበት። በሌላ በኩል የትራንስፖርት ዘርፉ የህዝብ ዓይን ያረፈበትና ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመው፤ ኅብረተሰቡ በዘርፉ ላይ ለሚያነሳቸው ችግሮች መፍትሄ እንዲሰጥ አሳስበዋል። የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታን ለማስፋፋትና በራስ አቅም መንገዶችን ለመገንባት የተከናወነውን ስራዎች መልካም እንደሆነ የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ በየጊዜው በዘርፉ ላይ ያለመናበብ ችግሮችና የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ በድክመት የሚታዩ ጉዳዮች መሆናቸውን አክለዋል። በትራንስፖርት ዘርፉ የሚነሱ ችግሮችን ለማስወገድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ቅንጅት በመፍጠርና ስምምነት በማድረግ የግንባታ ስራዎች እንዲፋጠኑ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። እንዲሁም ለመንገድ ጥገና እየወጣ ያለው በጀት ከፍተኛ በመሆኑ ጥገና በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያለው ኅብረተሰብ መሰረተ ልማቱን እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። የመንገድ ደህንነትና ጥበቃን "ክልሎች በባለቤትነት እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል"ያሉት አቶ አሸናፊ፤ አፈፃጸሙን ለመገምገም የሚያስችል አሰራር መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ መጨናነቅ ችግርን ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አመልክተዋል። የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው የዕቅዱ መነሻ የሆኑት በበጀት ዓመቱ ሁለተኛ ሩብ ዓመት የተያዙ ተግባራትን ለመፈፀም ማነቆ የሚሆኑ ጉዳዮችን መፍታት እንደሆነም አስረድተዋል። እንዲሁም የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት ያሉባቸውን ውስጣዊና ውጫዊ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በአጭር ጊዜ ለመፍታት የዕቅዱ መነሻዎች እንደሆኑም አብራርተዋል። ሚኒስቴሩ ዕቅዱን በተሰጠው ግብረ መልስ መሠረት አስተካክሎ በሁለት ቀናት ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው እንደሚያቀርብም ወይዘሮ ዳግማዊ ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ በመቶ ቀናት ውስጥ የትራንስፖርት ፖሊሲን ማጠናቀቅና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ማውጣት እንዲሁም የአቪዬሽን ፖሊሲና አዋጅ ጥናት በመከለስ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ አቅዷል። እንዲሁም ሚኒስቴሩን ለስራ ምቹና ሳቢ ለማድረግ፣ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅምን ለማሳደግ በተጨማሪም በዘርፉ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ የዕቅዱ አካል ነበሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም