የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለሀገሪቱ ሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

55
ጋምቤላ ታህሳስ 8/2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች አንድነት በማጠናከር ለሀገሪቱ ሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡ የሰላም አምባሳደር እናቶች ጠየቁ፡፡ የሰላም አምባሳደሮቹ ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሰራተኞች ጋር በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ተወያይተዋል፡፡ በዚህ ወቅት የሰላም አምባሳደር እናቶች እንዳሉት በተማሪዎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት በተቋማቱ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲከናወን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል፡፡ የሰላም አምባሳደሮቹ የቡድኑ አስተባባሪ ወይዘሮ ገነት አሰፋ ባስተላለፉት መልዕክት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች አስፈላጊውን እውቀት ይዘው እንዲወጡ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ ለዚህም ዋነኛ ተዋናይ ተማሪው መሆኑን ጠቁመው የሰላም አምባሳደር እናቶች ዓላማም  በየአካባቢው የሚነሱ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመፍታት ለሀገራችን አንድነት መጠናከር የድርሻቸውን ለመወጣት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች ከወላጆቻቸው በተለይም ከእናቶች የተቀበሉትን አደራ በመወጣት ነገን የተሻለ ለማድረግ ለሰላም መስፈን የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡ "በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲኖር ከተማሪዎች ባሻገር የግቢው አመራር አካላት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባል " ያሉት ደግሞ የቡድኑ አባል ወይዘሮ አዱኛ አህመድ ናቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም በበኩላቸው በመካከላቸው የሚነሱ አለመግባባቶችን በመፍታት ለዩኒቨርሲቲው ብሎም ለሀገሪቱ ሰላም የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ተጠሪ ተማሪ ገልገሎ ሚዲክሳ በሰጠው አስተያየት ከዚህ በኋላ በግቢው በተማሪዎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡ " በተለይም እያንዳንዳችን ወደዚህ ግቢ ስንመጣ ቤተሰቦቻችን  ከኛ የሚጠበቁትን ተስፋ ለማሳካት ትኩረት እናደርጋለን" ብሏል፡፡ "በቀጣይ ክፍተቶች ቢኖሩም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመፍታት ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ለዩኒቨርሲቲው ሰላም መጠበቅ የበኩላችንን እናደርጋለን " ያለው ደግሞ ተማሪ ወለላው አማረ ነው፡፡ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያየዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሰኬታማነት ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህብረሰብ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ሴት የሰላም አምባሳደሮቹ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ለሁለት ቀናት ሲያካሄዱ የቆዩትን ውይይት ትናንት አጠናቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም