በካማሽ ነዋሪዎች የሸቀጣ ሸቀጥና የእህል አቅርቦት ማነስ አፋጣኝ መፍትሄ ይፈልጋሉ

102
አሶሳ ታህሳስ 8/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የካማሽ ከተማ እየተረጋጋ ቢሆንም፤ የሸቀጣ ሸቀጥና የእህል አቅርቦት ማነስ በአፋጣኝ እንዲፈታላቸው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ካማሽ ከሦስት ወራት በኋላ ወደ ሰላምና መረጋጋት እየተመለሰች መሆኗንም መስክረዋል። በመንገድ እጦት በአሶሳ ከተማ የተከማቸው ከ4 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር፣ ዘይት፣ ዱቄትና ሌሎችም ሸቀጣሸቀጦች ሰሞኑን ወደ ካማሽ ዞን እንደሚጓጓዙ የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታውቋል፡፡ ከነዋሪዎቹ  አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በስልክ እንደተናገሩት በከተማው ሰላምና መረጋጋት እየተመለሰ ቢሆንም፤ የእህልና ሸቀጣ ሸቀጦች እጥረት ባለመቃለሉ ችግር ውስጥ ወድቀዋል። በከተማው የቀበሌ 02 ነዋሪ ወይዘሮ ስለእናት ትግሬ የከተማው ጸጥታ እየተረጋጋ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡''ይሁንና አሁንም ምንም ሸቀጣሸቀጥ፣ እህልና ሌሎችም የዕለት ፍጆታዎች ወደ አካባቢው እየገቡ አይደለም '' ብለዋል፡፡ ነዋሪዎች መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ለማግኘት መቸገራቸውን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዋ፣በተለይም ህጻናት፣ ነፍሰጡር እናቶች፣ አዛውንትና አቅመ ደካሞች የችግሩ ዋነኛ ተጠቂ ናቸው ይላሉ፡፡ችግሩ በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈለግለትም ጠይቀዋል፡፡ አቶ ድንቃ ጉዲና የተባሉ ሌላው የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው “ካማሽ ከተማ ሠላሟ የተመለሰ ቢሆንም፤ ነዋሪዎቿ ግን በምግብ እጦት አካባቢውን ለቀው ለመውጣት እያሰቡ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አልማሂ ምርቱ ከአሶሳ ወደ ካማሽ ያለው መንገድ ከትናንት ጀምሮ በመከፈቱ ምርቱን ለሕዝቡ ሰሞኑን ለማከፋፈል ተሽከርካሪዎች እየተፈለጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። በዚህም 1ሺህ 800 ኩንታል ዱቄት፣ 1ሺህ 620 ኩንታል ስኳርና 195 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት ይጓጓዛል ብለዋል። ምርቱ ቀደም ሲል በከተማው በሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት አማካይነት ተገዝቶ አሶሳ ላይ ተከማችቶ  የቆየ እንደነበርም አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም መንገድ በተዘጋበት ወቅት በቢላ ከተማ ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ያለአግባብ የተራገፈውን ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ዘይት ለማስለቀቅ ቢሮው ከአስተዳደር አካላት በመነጋገር ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ቢሮው በክልሉ በመንገድ መዘጋት ሳቢያ የታየው የዋጋ ጭማሪ ወደ ነበረበት እንዲመለስ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ መሐመድ ገለጻ  አግባብ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ የንግድ ሱቆችን ከማሸግና ከገንዘብ መቀጮ ባለፈ ፍርድ ቤት እስከ ማቅረብ ሊደርስ ይችላል፡፡ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የምዕራብ ዕዝ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ሳቢያ የተዘጉ መንገዶች ከትናንት ጀምሮ አገልግሎት መጀመራቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም