የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለአፍሪካ ዕድገት በፖሊሲ የተመራ ድጋፍ በማድረግ ላይ ነው

94
አዲስ አበባ ታህሳስ 8/2011 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ለአፍሪካ ሰላም፣ ዕድገትና ዴሞክራሲያዊ ግንባታ በፖሊሲ የተመራ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1958 የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ የተመሰረተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን /ኢሲኤ/ 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ተከብሯል። በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው ዓለም አቀፍ ድርጅትን በአዲስ አበባ የመሰረቱት ለቅኝ ገዥዎች አልበገር ያለችውን ኢትዮጵያን ጨምሮ ላይቤሪያ፣ ጋና፣ ሞሮኮ፣ ሱዳን፣ ቱኒዚያና ግብጽ ናቸው። የተቋሙ ምስረታ የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ለማፋጠንና አንድነታቸውን ለማጎልበት በስራ ዕድል ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሰው ኃይል ልማትና በአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉት፤ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አፍሪካን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በሰላም ጉዳዮች ውጤታማ ትብብር እንዲኖራቸው አግዟል። ከዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጋር በማስተዋወቅ ረገድ ነጻ የንግድ ቀጠና ምስረታ ሂደትና አፍሪካውያን የተፈጥሮ ሐብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማነሳሳት ተቋሙ የተጣለበትን ኃላፊነት አንደተወጣም ገልጸዋል። የአፍሪካ ኀብረት አጀንዳ 2063 እና የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲፈጸሙ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በፖሊሲ የተመሰረተ የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አቶ ደመቀ ገልጸዋል። በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በዴሞክራሲያዊ ግንባታ፣ በውጤታማ የፋይናንስና የተፈጥሮ ሐብት አስተዳደር እንዲሁም በቀጣናዊ ሰላም ማስፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል። እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጻ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በርካታ ተግባራትን ማከናወን ቢችልም በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በድህነት አዘቅት ውስጥ ይኖራሉ። ''የትናንት የአፍሪካ መሪዎች ትልቅ ራዕይ ሰንቀው በተግባር ላይ ያዋሉትን ተቋም እኛ ደግሞ ድህነትን ለማጥፋት፣ ዴሞክራሲ ለመገንባት፣ ሰላም ለማስፈን ከትናንት መሪዎቻችን መማር ይገባል'' ብለዋል። ከቀደሙት የአፍሪካ መሪዎች ቁርጠኝነትን በመማር ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች አፍሪካን ማቆየት እንደሚገባም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ቬራ ሶንግዌ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ባለፉት 60 ዓመታት ለአፍሪካ አንድነትና ዕድገት ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ በአሁኑ ወቅትም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። በአፍሪካ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን በላይ ዜጎች ያሉ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ፀሐፊዋ ኢኮኖሚያቸው ሁለት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ዶላር የደረሰ በመሆኑ ያለውን ሐብት በቅንጅትና በትብብር ስራ ላይ ማዋል እንዳለባቸው ገልጸዋል። በዘላቂ የልማት ግቦች ድህነትን በመቀነስ ረሃብን ለማጥፋት የተያዘው ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ በአፍሪካውያን መካከል ያለው የንግድና የገበያ ትስስር ማደግ እንደሚገባም አመልክተዋል። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከአፍሪካ ኀብረትና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የዘላቂ ልማት ግቦች ስራ ላይ ውለው ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት እንዲሁም ልማት የተረጋገጠባት አፍሪካን ለማየት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ቬራ ሶንግዌ ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም