በሌተናል ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ ላይ ተጨማሪ የሙስና ወንጀል ማግኘቱን ፖሊስ ገለጸ

75
አዲስ አበባ ታህሳስ 8/2011 በሌተናል ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ ላይ ተጨማሪ የሙስና ወንጀል ማግኘቱን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ገለጸ። የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ሌተናል ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ ከዚህ ቀደም በህዳር ወር ላይ የዐቃቤ ህግ የምርመራ ሂደትን በማደናቀፍ (ሰነድ ማስጠፋት) ተጠርጥረው ነበር የተያዙት። ዛሬ መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው ተጠርጣሪ ላይ ተጨማሪ የሙስና የወንጀል ድርጊት በማግኘቱ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ 14 ቀናት ተፈቅዶለታል። ተጠርጣሪው በዛሬው ችሎት የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ኩባንያ በሆነው ሃይቴክ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የሰው ሃብት አስተዳደር ሆነው በሚያገለግሉበት ወቅት ስራ አስኪያጁ ለስራ ጉዳይ በሌሉበት ወቅት ውክልና ተሰጥቷቸው ሳለ በአፋጣኝ የኩባንያውን ማኔጅመንት በማሳመን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ትራንስፎርመር እንዲያቀርብ የግዥ ውል ይፈራረማሉ። ነገር ግን ወልዳይ ገብረማርያም ብቸኛ አስመጪ በሚል ያለምንም ጨረታ ከ85 ሚሊዮን 783 ብር በላይ ግዥ በመፈጸም በመንግስትና ህዝብ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በሚል ፖሊስ በሙስና ወንጀል የጠረጠራቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። ፖሊስ ለዚህ ጥርጣሬው በቂ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ያለው በመሆኑ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን ጠይቋል። የተጠርጣሪ ጠበቃ አዳዲስ ነገሮችን በማምጣት ሌላ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ ተገቢ አይደለም በማለት ተጨማሪ ጊዜ እንዳይሰጥ ተከራክረዋል። በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ከታህሳስ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የሚታሰብ 14 የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለታህሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ከዚህ ቀደም የብርጋዴር ጀኔራል አድጎ ገብረጊዮርጊስ ጸሃፊን በማስገደድ ማስረጃ እንዲጠፋ አድርገዋል በሚል ፖሊስ ጠርጥሯቸው የነበሩት ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ ላይ በተጨማሪ የሙስና ወንጀል የጠረጠራቸው መሆኑን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ መግለጹ ይታወሳል። ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፤ ተጠርጣሪው ኮሎኔል ሰጠኝ 'ኮሞቹ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ' የተሰኘ ተቋም የሰው ሃብት ልማት ሃላፊ ሆነው እያለ ህጉን ያልተከተለ የ15 ሚሊዮን ብር ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ በአገርና በህዝብ ንብረት ላይ ጉዳት እንዳደረሱም ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም