የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስከሬን ረቡዕ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በሚሌኒየም አዳራሽ ህዝባዊ ሽኝት ይደረጋል

70
አዲስ አበባ ታህሳስ 8/2011 የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስከሬን ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በሚሌኒየም አዳራሽ ህዝባዊ ሽኝት ይደረግለታል። ፕሬዚዳንቱ ለአገራቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚመጥን የቀብር ስነስርዓት ለማካሄድ ብሔራዊ የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል። የኮሚቴው የህዝብ ግንኙነት አቶ መለስ አለም እንደገለጹት፤ ለቀድሞ ፕሬዚዳንት አስከሬን ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ሽኝት ይደረግለታል። ከዛሬ 10 ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ በቀድሞ ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት በመገኘት በተዘጋጀው ሰነድ ላይ የሀዘን መግለጫቸውን የሚያሰፍሩበት መዝገብ ተዘጋጅቷል ብለዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ በተወለዱ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ታህሳስ 5 ቀን 2011 ሌሊት ነው። አቶ ግርማ ከአንድ ዓመት በፊት በሞት ከተለዩአቸው ባለቤታቸው አምስት ልጆችን አፍርተዋል። አቶ ግርማ ከ1994 እስከ 2006 ዓም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልገለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም