ማህበሩ የኅብረት ሥራ ማህበራት አቅምን ለማጎልበት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ሰጠ

130
ሶዶ ታህሳስ 8/2011 የወላይታ ልማት ማህበር የመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራትን አቅም ለማጎልበት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር አከፋፈለ። ማህበሩ ከጣሊያን መንግሥት ለአምስት ዓመታት ውስጥ የኅብረት ሥራ ማህበራትንና ዩኒየኖችን አቅም የሚያሳድግበት የ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ማህበሩ ካገኘው ድጋፍ ለመጀመሪያው ዙር የተለቀቀውን ብድር  ከአምስት ወረዳዎች የተመረጡት 17 ማህበራት ሰሞኑን ወስደዋል፡፡ የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ጢሞቴዎስ ማህበሩ ለአርሶ አደሩ የግብርና ግብዓቶች በማቅረብና የክህሎት ማሳደጊያ ሥልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የኅብረት ሥራ ማህበራት ከማህበሩ በሚያገኙት ድጋፍ የአርሶ አደሩን ምርት ተረክበው በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥ ገበያን እንዲያረጋጉና ገቢያቸውም እንዲጎለብት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ማህበራቱን ባገኙት ከወለድ ነጻ ብድር ግብዓቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ትርፋማ እንደሚያደርጋቸው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ማህበራቱ ብድሩን በተቀመጠላቸው ጊዜ በመመለስ ሌሎች ማህበራት እንዲጠቀሙበት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አማካሪ ሚስተር አልበርቶ ሞአይ በበኩላቸው የጣሊያን መንግሥት የማህበራቱን አቅም ለማሳደግ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል። ማህበሩ የማህበራቱን አቅም በገንዘብ በመደገፍ ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ  ያለው ተግባር አበረታታች ነው ብለዋል፡፡ ማህበራቱ የሕዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የወላይታ ዞን ኅብረት ሥራ ማህበራት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ገቺሬ ናቸው፡፡ ማህበራቱ ባለባቸው የገንዘብ እጥረት አባላትን በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከኪንዶ ኮይሻ ወረዳ የኦይዱ ጫማ መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ገብረመድህን አዴቶ እንዳሉት ማህበሩ የአርሶ አደሩን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ተረክቦ ለአካባቢው ነዋሪዎች በማቅረብ ገበያ ለማረጋጋት የነበረውን ሚና ገድቦት መቆየቱን ተናግረዋል። ብድሩ ለአርሶ አደሩ ግብዓቶችን ለነዋሪዎች ደግሞ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ያስችለዋል ብለዋል፡፡ በዞኑ ከአንድ ሺህ በላይ ማህበራት ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም