በሰሜን ሸዋ ዞን ከ75ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር በዚህ ዓመት ይመረታል

72
ደብረ ብርሃን ታህሳስ 8/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከ75ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር በዚህ ዓመት እንደሚመረት የዞኑ ግብርና  መምሪያ ገለጸ። በዞኑ በምርጥ ዘር ብዜት በተሰማሩ 4ሺህ 477 አርሶ አደሮች ለምቶ በመኸር ወቅት ልማት እንደሚውል በመምሪያው የሰብል ልማት ጥበቃ የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ የሥራ ሂደት መሪ አቶ አበበ ጌታቸው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታውቀዋል። ስንዴ፣ ገብስ፣  ጤፍ፣ ማሽላና ማሾ የሚገኙበት ዘር  65ሺህ 353 ሄክታር መሬት ለማምረት እንደሚያስችል አስረድተዋል።ከነዚህም  60 ከመቶ ደግሞ በክልሉ ግብርና ቢሮ     አማካይነት ለሌሎች አካባቢዎች፣ቀሪው  ለአካባቢዉ አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርብላቸዋል  ብለዋል። የአርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ ምርጥ ዘር ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት አርሶ አደሮች ጥራቱን ጠብቀው በማምረት ለዘር ተቀባይ ድርጅቶች እንዲያቀርቡ አቶ አበበ ጠይቀዋል። የተጉለት ዘር ብዜትና ግብይት ኅብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን ገብረጊዮርጊስ በበኩላቸው በዚህ ዓመት በ370 ሄክታር መሬት ላይ 660 አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም  ስንዴና  የቢራ ገብስ  ዘር ማባዛታቸውን ገልጸዋል። አርሶ አደሮቹ  22ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር እንደሚያመርቱ መረጋገጡንም አመልክተዋል። በሞረትና ጅሩ ወረዳ ቦሎ ዘር ብዜት ኅብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ መቶ አለቃ ሰፋልኝ አበበ  የማህበሩ አባላት በ64 ሄክታር መሬት ላይ የዳቦና የመኮረኒ ስንዴ እንዲሁም የቢራ ገብስ ምርጥ ዘር ማልማታቸውን ተናግረዋል። ከዚህም 1ሺህ 408 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። በሲያደብርና ዋዩ ወረዳ አርሶ አደር በቀለ አደሬ በበኩላቸዉ ባለፈው የምርት ዘመን ባላቸው አንድ ሄክታር መሬት 43 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር አምርተው 50ሺህ 800ብር ገቢ አግኝቼያለሁ ብለዋል። በዚህ ዓመትም ከዚሁ መሬት ከ50 ኩንታል በላይ በማምረት የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ለዞኑ አርሶ አደሮች በ2011/12 የምርት ዘመን 14ሺህ 800 ኩንታል ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልግ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከዞኑ በ2010/11 ምርት ዘመን በ499ሺህ 986 ሄክታር መሬት ከለማው ሰብል እስካሁን በ70ሺህ 629 ሄክታር ያለው ሰብል ተሰብስቧል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም