የዞኑ ምክር ቤት የክልል እንሁን ጥያቄን ተቀብሎ አፀደቀ

1618

ሶዶ ታህሳስ 8/2011 የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የክልል እንሁን ጥያቄን ተቀብሎ  በሙሉ ድምጽ አጸደቀ፡፡

ምክር ቤቱ ጥቅምት 29 እና 30 2011 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ የክልል እንሁን ጥያቄን ተቀብሎ የህዝብ ይሁንታን ለማረጋገጥ ለአስፈጻሚ አካላት ውክልና ሰጥቶ ነበር፡፡

ይህን ተከትሎ በወረዳና በቀበሌ ምክር ቤቶች እንዲሁም በህዝብ መዋቅሮች ምክክር ተደርጎበት በሙሉ የህዝብ ይሁንታ ማግኘቱ ተመልክቷል፡፡

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደጋቶ ኩምቤ ኃላፊነቱን ከተቀበሉ ጀምሮ የነበረውን የህዝብ የውይይት መድረኮችና ሂደቱን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ጉባኤ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው  እንዳሉት የወላይታ ህዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ ረጅም ጊዜ ያስቆጠና  ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው ነው፡፡

ዞኑ ክልል ሲሆን ህዝቡ ባህል፣ ወግና ማንነትን በመጠበቅና  በማሳደግ  ተወዳዳሪነትን  ለመጨመር የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተበታትነው የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ ለመከላከል በክልል መደራጀት ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግርን ለመፍታት  እንዲሁም የተማረ የሰው ኃይልን በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችልም  አመልክተዋል፡፡

የዞኑ ምክር ቤት በዞኑ አስተዳዳሪ የቀረበውን ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ  የክልል እንሁን ጥያቄውን  በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የጸደቀውም ለክልሉ ምክር ቤት እንደሚቀርብ ተጠቁሟል፡፡