በምዕራብ ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር መፈታቱ ተገለጸ

96
አሶሳ ታህሳስ 7/2011 በምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ሲያጋጥም የነበረው የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ችግር መፈታቱን በመከላከያ ሰራዊት የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ አስታወቁ። ዋና አዛዡ ሜጀር ጀኔራል አስራት ደኔሮ ለኢዜአ እንደገለጹት በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልል አጎራባች አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች የፈጠሩት የጸጥታ ችግር በህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። ከዚህ በተጨማሪ ከአሶሳ አዲስ አበባ፣ ከነቀምት አዲስ አበባ፣ ከነቀምት አሶሳ እና ከነቀምት ቡሬ መስመር የንግድና የትራንስፖርት መስተጓጎል ሲያጋጥም መቆየቱን ተናግረዋል። “ችግሩን ያስከተሉት የታጠቁ ሃይሎች ከሃገር መከላከያ ሠራዊት አቅም በላይ ሆነው አይደለም” ያሉት አዛዡ የብሄራዊ ጸጥታ እና ደህንነት ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ሰሞኑን የምዕራብ እዝ ሃይል አካባቢውን መቆጣጠሩን አስረድተዋል። ሠራዊቱ ከሁለቱ ክልሎች ጋር በመተባበር ባካሔደው የተጠናከረ ፍተሻ አካባቢው መረጋጋቱን ገልጸው በአማራ ክልል ከቅማንት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የተከሰተው የጸጥታ ችግርም ካለፉት ሁለት ሣምንታት ወዲህ ወደ ሰላም መመለሱን ተናግረዋል። ለተገኘው ውጤት የህብረተሰቡ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰው ሠራዊቱ እስከ ህይወት መሥዋዕትነት እንደከፈለም አዛዡ ጠቁመዋል፡፡ የግጭቶቹ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚደረገውን ጥረት መደገፍ የሰራዊቱ ትኩረት መሆኑን ጠቁመው ከየአካባቢው አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስና የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈም ሃገሪቱ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር በኩል የሚከሰተውን ህገ-ወጥ የሰዎች እና የጦር መሣሪያ ዝውውር በትኩረት እየተከታተለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም