ተቋማቱ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ህልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

68
አዲስ አባባ ታህሳስ 7/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮዽያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ አመራር ቦርድ፣ ማኔጅመንትና ሠራተኞች  በቀድሞው የኢፌዲሪ  ፕሬዚዳንት ክቡር ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እረፍት ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማቸው ለኢዜአ የተላከ መግለጫ አመልክቷል። ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ አመራር ቦርድ አባል ሆነው ማገልገላቸውንም መግለጫው  አስታውሷል፡፡ የኢትዮዽያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በበኩሉ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የቀድሞ ፕሬዚደንት ግርማ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ1942 እስከ 1950 ዓ.ም ድረስ ለዘጠኝ አመታት አገልግለዋል። አቪዬሽኑ በመግለጫው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ እንደነበሩም አውስቷል። በባለስልጣኑ በተለያዩ የስራ ክፍሎች ከሃላፊነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነት ደረጃና የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ሃላፊም በመሆን ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበራቸውም  ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል፡፡ የባለስልጣኑ ሰራተኞችና የማኔጅመንት አባላት በፕሬዚዳንቱ  ህልፈተ ህይወት ሃዘን እንደተሰማቸው ያመለከተው መግለጫው በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽዎ ታሪክ ሁሌም ሲያወሳቸው እንደሚኖር ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም