4ኛው የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ጉባኤ በመቐሌ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው

56
መቐለ ታህሳስ 7/2011 4ኛው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሴቶች ሊግ ጉባኤ በመቐሌ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው። የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ በ2002 ዓ.ም ተመስርቶ አሁን ላይ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሴት አባላትን ያቀፈ ነው። ሊጉ በየሁለት ዓመቱ ጉባኤውን የሚያካሂድ ሲሆን የአሁኑ  4ኛ ጊዜ ነው ። ”የተደራጀ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የዘንድሮ የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ጉባኤ እየተካሄደ ያለው። በጉባኤው የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ሊቀመንበር እና የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል፣ የፌዴሪሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም እንዲሁም ከየክልሉ የመጡ የሊጉ አባላት ተገኝተዋል። ከታህሳስ 7 እስከ 9 ቀን 2011 ዓ.ም በሚቆየው በዚሁ ጉባኤ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። 3ኛው የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ መደበኛ ጉባኤ በ2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም