በቀዶ ህክምና 120 ሚስማሮች የወጣለት ታካሚ ህክምናውን አጠናቀቀ

105
አዲስ አበባ ታህሳስ 7/2011 አንድ መቶ ሃያ ሚስማሮችና የተለያዩ ባእድ ነገሮች ከሆዱ በቀዶ ህክምና የወጣለት ታካሚ ህክምናውን አጠናቆ በነገው እለት ከሆስፒታል እንደሚወጣ የቅዱስ  ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ። ታካሚው 120 ሚስማሮች እንዲሁም መርፌ ቁልፍና የጠርሙስ ስባሪዎች ጥቅምት 10 ቀን 2011 ዓ.ም በቀዶ ጥገና እንደወጣለት የሚታወስ ነው። 2፡30 የፈጀው የቀዶ ህክምና ሰባት የህክምና ባለሙያዎች ተሳትፈውበት የተካሄደና በስኬት የተጠናቀቀ ነበር ። ይሁን እንጂ ታካሚው የአዕምሮ ህመምተኛ በመሆኑና ተጨማሪ  የህክምና ክትትል ስላስፈለገው ለሁለት ወራት ያህል በሆስፒታሉ ቆይቷል ። በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ዳዊት ታዓረ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አንድ መቶ ሃያ ሚስማሮችና የተለያዩ ባዕድ ነገሮች በሆዱ ውስጥ  የነበረው ታካሚ ህክምናውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቆ  ከሆስፒታሉ በነገው ዕለት ይወጣል። ታካሚው  ወደ ህክምና ተቋም ሲመጣ የነበረበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪና ህይወቱን ለማትረፍ  የነበረው እድል ጠባብ  እንደነበረም አስታውሰዋል። ወደ ሆስፒታል ሲመጣ በከፍተኛ የጤና ችግር ውስጥ የነበረው ታካሚው በአሁኑ ወቅት ጤንነቱ በመልካም ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከሆስፒታል እንደሚወጣም ነው ያስረዱት። ታካሚው 'አኩፊጂያ' በተባለ የአእምሮ ህመም ላለፉት አስር አመታት ተጠቂ መሆኑን በመግለጽ ለስምንት ዓመታት የአእምሮ መድሃኒት ሲወስድ መቆየቱንም ገልጸዋል። ታካሚው በበኩሉ አሁን በጥሩ ጤንነት ላይ መሆኑን ገልጿል። እንደ ዶክተሩ ገለጻ ፤ የአእምሮ ህሙማኖች መድሃኒታቸውን እንዳያቋርጡና በሽታው እያገረሸ ለባሰ የጤና እክል እንዳይጋለጡ ቤተሰብ፣ በማህበረሰቡ፣ በጤና ባለሙያዎች ጥብቅ ክትትል እንድሚያስልጋቸው አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም