የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዜጎች ሞትና ጉዳት እንዲቆም ጠየቁ

61
ሐረር ታህሳስ 7/2011 መንግሥት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን  ሞትና ጉዳት እንዲያስቆም የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠየቁ። ተማሪዎቹ ከያዟቸውና ካስተጋቡባቸው መፈክሮች ''መፈናቀል ይቁም!''፣በብሔር ግጭት የሚፈጥሩ አካላት ለሕግ ይቅረቡ!''፣የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በብሔር ለማጋጨት የሚሞክሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው ይቆጠቡ!'' የሚሉ ነበሩባቸው። ተማሪዎቹ ሰሞኑን በሞያሌ ከተማ በታጣቂዎች ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ኅዘናቸውን በገለጹበት ወቅት እንዳመለከቱት መንግሥት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ሞት፣የአካልና የንብረት ጉዳት እንዲገታ ማድረግ አለበት፡፡ ከተማሪዎቹ መካከል የአራተኛ ዓመት የሕግ ተማሪ ኦብሲቱ ዱባ ''በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲሰፍን የበኩላችንን እያበረከትን እንገኛለን፤ መንግሥትም በዜጎት ሕይወት ማጥፋትና መፈናቀልን በሚፈጽሙ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ ሊወስድ ይገባል” ትላለች። መንግሥት የጀመረው የለውጥ ጉዞ ያልተመቻቸው አንዳንድ አካላት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በድንበር አካባቢዎች ላይ ግጭት በመፍጠር የዜጎች ሕይወት የሚያጠፉና ከመኖሪያቸው በሚያፈናቅሉ አካላት ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ተማሪ ሙፍቲ መንዛ ጠይቋል። የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ መሐመድ አህመድ ዳውድ ግጭቶች በማቀድ፣ ሁከትና ግርግር በመፍጠር ፖለቲካን ማራመድ ፀረ ሰላም ተግባር በመሆኑ መንግሥት ጉዳዩን በመከታተል በአጥፊዎች ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት ብሏል። የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አንድነታቸውን በማጠናከር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራቸውን በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ ተናግሯል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎችን በብሔር በመከፋፈል ግጭት ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን እንቅስቃሴ ለመግታት  የሚደረገው ጥረት እንዲጠናከር የጠየቀችው የሦስተኛ ዓመት የአካውንቲንግ ተማሪ ከሪማ መሐመድ ናት። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በያዝነው የትምህርት ዘመን 27ሺህ ያህል ተማሪዎችን በመደበኛ፣በርቀት፣በተከታታይና በክረምት መርሐ ግብሮቹ በማስተናገድ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም