በሀዋሳ የተገነባው ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከል ተመረቀ

62
ሀዋሳ ታህሳስ 6/2011 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከ21 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በሀዋሳ ከተማ ያስገነባው ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከል ዛሬ ተመረቀ፡፡ በምረቃ ስነስርዓቱ ወቅት የንግድና ኢንድስትሪ ሚንስትሯ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት አርሶ አደሩ ባለፉት ዓመታት ምርቱን ለማዘጋጀት ጊዜና ጉልበት በማይተካ ሁኔታ  ነጋዴ በሚያቀርብለት ዋጋ  ለመሸጥ ሲገደድ ቆይቷል፡፡ ይህንን የግብይት ስርዓት ለመቀየር መንግስት የተለያዩ ስትራተጂዎችና ፖሊሲዎችን በማውጣት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ባከናወነው ተግባር ዋጋ ተቀባይ ብቻ ሳይሆን ዋጋ ተማኝ መሆን እንደቻለ ተናግረዋል፡፡ ሀገሪቱ ወደ ውጪ የምትልካቸው ምርቶች ደረጃቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ  የሚቀበሉ ሀገራት እምነት እንዲያድርባቸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው በዋናነት ለውጪ ገበያ የሚቀርብ ቡና በብዛትና ጥራት አምርቶ ለገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስት በቡና የሚሸፈን ማሳን መጠን በማስፋትና የምርታማነት ማሻሻያ ፓኬጆችን በአግባቡ ስራ እንዲውል አቅጣጫ ማስቀመጡንም ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ እንደገለጹት መንግስት ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ለመፍጠር የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ስራ እንዲጀምር ካደረገበት ጊዜ አንስቶ  አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻልና ለማሳደግ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም በአካል በመገኘት ይፈጸም የነበረው ግብይት ወደ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስርዓት ማደግ ችሏል፤ ይህም በርቀት በመሆን መገበያየት እንደሚቻል ነው፡፡ ከአስር ዓመት በፊት በአንድ ማዕከል አንድ ዓይነት ምርት ብቻ በመቀበል ስራ የጀመረው የምርት ገበያው ዛሬ ሰባት የግብርና ምርቶችን በ22 ማዕከላት መቀበል እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ ይህን ስርዓት ከዘረጋ ጊዜ ጀምሮ ባሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ አንድ ሚሊዮን 900ሺህ ቶን ቡና፣ ሰሊጥ ቦሎቄና ማሾ በማገበያየት ከ81 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት እንደቻለም ጠቁመዋል፡፡ የሀዋሳ የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከል ባለፉት ሁለት ወራት የሙከራ ስራውን ሲያከናውን እንደቆየና በዚህም ጊዜ 316 ቶን ቡና ለገበያ በማቅረብ 22 ሚሊዮን ብር ገቢ ማስገኘት እንደቻለ በምረቃው ስነሰርዓት ወቅት ተገልጿል፡፡ ማዕከሉ ለደቡብና ለኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በስራ አጋጣሚ ከተለያዩ አካባቢ ወደ ሀዋሳ የሚመጡ ነጋዴዎች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ለግንባታው ከዋለው ወጪ ውስጥ አራት ሚሊዮን 800ሺህ ብር የተሸፈነው በአውሮፓ ህብረት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተመሳሳይ  የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እያስገነባ ነው፤ ከነዚህም መካከል የነቀምቴና የሁመራው ዘንድሮ ወደ ስራ ይገባሉ ተብሏል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም