ሳሳካዋ ግሎባል 2000 ለግብርናው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል... ግብርና ሚኒስቴር

77
አዳማ ታህሳስ 6/2011 ሳሳካዋ ግሎባል 2000 የኢትዮጵያ ግብርና አሁን ለደረሰበት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ግብርናውን በቴክኖሎጂ፣ በአቅም ግንባታና በተቀናጀ ኤክስቴንሽን ለማጠናከር የሚረዳ ስትራተጂክ እቅድ ማዘጋጀቱን ሳሳካዋ ግሎባል 2000 አስታውቋል ። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ለኢዜአ እንዳሉት ሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት ከግብርና አመራሮች፣ ከባለሙያዎች፣ ከአርሶ አደሮችና በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር በቅርበት በመስራት ለግብርናው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የሀገሪቱን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ እንቅስቃሴ ለማጠናከርና ከምርት እስከ ግብይት ድረስ ያለውን የእሴት ሰንሰለት ለማዘመን ያደረገው ድጋፍም እንዲሁ። መንግስት የግብርናው ዘርፍ የበለጠ ለማዘመንና ከኢንዱስትሪው ጋር ያለው ተመጋጋቢነት ለማጠናከር አዲስ ስትራተጂክ እቅድ እያዘጋጀ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዝግጅት ወቅት ሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ከሚገኝበት ደረጃ የሚጣጣም የራሱ የሆነ የአምስት ዓመት ስትራተጂክ እቅድ ማሰናዳቱ ተገቢና ወቅታዊ  በመሆኑ እንደሚደገፍ አመልክተዋል። የሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ፋንታሁን መንግስቱ በበኩላቸው " አሁን የተዘጋጀው የአምስት ዓመት ስትራተጂክ እቅድ በመጀመሪያው ዓመት በ5 ሚሊዮን ዶላር የሚጀመርና በጀቱ በየዓመቱ እያደገ የሚሄድ ነው "ብለዋል ። ይኽው ሶስተኛው ምዕራፍ ስትራተጂክ እቅድ 90 ሺህ አርሶ አደሮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው በጥራት አምርተው ለኢንዱስትሪ እንዲያቀርቡና ወደ ማቀነባበር እንዲሸጋገሩ ብሎም የምርት ብክነትን እንዲቀንሱ የሚያስችል ድጋፍ ያደርግላቸዋል ። ዶክተር ፋንታሁን እንዳሉት እቅዱ በሀገሪቱ  ከሚገኙ ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የግብርና ትምህርትና የግብርና ኤክስቴንሽን አቅም ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ሁሉንም የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በ60 ወረዳዎች ላይ ከማምረት እስከ ተጠቃሚው ድረስ የሚዘልቅ ሞዴል የእሴት ሰንሰለት የልህቀት ማዕከል ለመገንባት መታቀዱንም ጠቁመዋል። ሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ምርታማነትን ለማሳደግ በበቆሎ ምርት ላይ መስራት የጀመረ ሲሆን ምርቱ አድጎ አርሶ አደሩ ገበያ በማጣቱ  ወደ እሴት ሰንሰለት በመሸጋገር ኤክስቴንሽኑን ሲደግፍ ቆይቷል። የኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አርሶአደሮች ተጠቃሚ ማድረጉን የተቋሙ ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር አንተነህ ግርማ ተናግረዋል። የሳሳካዋ ግሎባል 2000 ኢትዮጵያ አዲሱ የአምስት ዓመት ስትራተጂክ እቅድ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ፣ የክልልና የፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ በአዳማ ከተማ ውይይት ተደርጎበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም