በየካ ክፍል ከተማ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ

71
አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2011 በአዲስ አበባ የካ ክፍል ከተማ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ 71 የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመረቁ። ፕሮጀክቶቹን በሥፍራው በመገኘት የመረቁት የከተማው ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ሰለሞን ኪዳኔ እና ሌሎች ኃላፊዎች ናቸው። ከፕሮጀክቶቹ መካከል የውስጥ ለውስጥ የጥርብ ድንጋይ መንገድ፣ የጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ሥራ ማስኬጃ  ሼዶች እንደዚሁም የወጣቶች መዝናኛዎች ይገኙበታል። ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ሰለሞን እንዳሉት አስተዳደሩ ነዋሪውን የምጣኔ ኃብታዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች በማከናወን ላይ ነው። በክፍለ ከተማው ዛሬ የተመረቁት አብዛኛዋቹ ፕሮጀክቶችም የተገነቡት መሰረተ ልማት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች በመሆኑ የአካባቢውን ህዝብ የቆየ የልማት ጥያቄ ይመልሳሉ ተብሎ እንደሚታመንም ጠቅሰዋል። ፕሮጀክቶቹ በተለይም በአዲስ መልክ በተቆረቆሩ ሰፋሮች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የጤና እና የትምህርት አገልግሎት ተደራሽነት የሚያጠናክሩ ናቸው ሲሉም ገልፀዋል። ፕሮጀክቶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ከግማሽ ወስዷል። በግንባታ ወቅትም ከ4 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም