በአፍሪካ ቀንድ ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር ለመፍጠር የተጀመረው ጥረት በህግ ማእቀፍ ሊደገፍ ይገባል ተባለ

47
አዲስ አበባ  ታህሳስ 6/2011 በአፍሪካ ቀንድ አባል አገራት መካከል ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር ለመፍጠር የተጀመረው ጥረት ውጤታማ  ይሆን ዘንድ ሂደቱ በህግ ማእቀፍ ሊደገፍ እንደሚገባው የምጣኔ ኃብት ምሁር አሳሰቡ። በቅርቡ በአካባቢው አገራት በተለይም በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መንግስታት መካከል ጠንካራ ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር የተደረሰው ስምምነት ለአካባቢው መረጋጋትና ልማታዊ እድገት ወሳኝ እመርታ ተደርጎ ተወስዷል። የተጀመረው ይህ ጥረት አገራቱ ያላቸውን ኃብት በማቀናጀት የጋራ እድገት ለማምጣት የሚያስችላቸው መሆኑን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ኦሶሲየሽን የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ፖሊሲ ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር አሰፋ አድማሴ ከኢዜአ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ገልፀዋል። እነዚህ አገራት ላለፉት ዓመታት በአንድም ይሆን በሌላ ጦርነት ውስጥ የቆዩ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ በጀት ለመከላከያ ኃይል ያወጡ እንደነበር የተናገሩት ዶክተር አሰፋ ይህም የአገራቱን ምጣኔ ኃብት እንደጎዳው ነው የተናገሩት። ሆኖም አሁን የተጀመረው የሰላም ግንባታ እንቅስቃሴ  አገራቱ ለመከላከያ ኃይል የሚመድቡትን ይህን ኃብት ለልማት እንዲያውሉት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑንም አስረድተዋል። ዶክተር አሰፋ እንደገለፁት በአፍሪካ ቀንድ አባል አገራት መካከል የሚታሰበው የምጣኔ ኃብት ትስስር የተሳካ እንዲሆን ግን የአገራቱ ህጎች፣ መመሪያዎችና ተቋማት መቀናጀት አለባቸው። አገራቱ በየግላቸው ማከናወን ከሚጠበቅባቸው የውስጥ ቅድመ ዝግጅ አንፃር በአካባቢው አገራት መካከል የሚታሰበው የምጣኔ ኃብት ትስስር  ጊዜ ሊወስድ ይችላል ያሉት ባለሙያው በመሆኑም ውጥኑ የየአገራቱን ያላሰለሰ ትጋት እንደሚጠይቅ አመልክተዋል። ከነዚህም መካከል ህጎችንና የአሰራር ደንቦችን ከሌሎች አገራት ጋር የተቀናጀና የተመሳሰለ ማድረግ፣ እነዚህን ህጎችና የአሰራር ደንቦች ወደተግባር የሚተረጉሙ ተቋማትን ማቋቋም ይገኙበታል ብለዋል። እንዲህ ማድረግ ደግሞ በአገራቱ መካከል በሁሉም ዘርፎች የሚኖረው የትብብር ግንኙነት ዘላቂነት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን ዶክተር አሰፋ ገልፀዋል። የተጀመረው ትስስርን የመፍጠር ሂደት ህጎችንና ተቋማትን በማቀናጀት ተግባር ከታገዘ በአካባቢው ጠንካራ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ሀሰን መሐመድ በበኩላቸው "በአፍሪካ ቀንድ አገራት አስተማማኝ መረጋጋትን ማምጣት በአገራቱ መካከል የምጣኔ ኃብት ትስስር ለመፍጠር ለተጀመረው ጥረት ስኬት ቁልፍ ጉዳይ ነው" ሲሉ ገልፀዋል። በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መካከል ጠንካራ የትብብር ግንኙነትና የተረጋጋ አካባቢ ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት ያደነቁት ምሁሩ ሆኖም አገራቱ የውስጥና የድንበር ጉዳዮቻቸውን በአፋጣኝ ለመፍታት የሚያስችል እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው መክረዋል። ከፍተኛ የህዝብ ቁጥርን ጨምሮ በተለያዩ የተፈጥሮ ኃብቶች የታደሉ አገራትን የያዘው የአፍሪካ ቀንድ ከ80 በመቶ የሚልቀው የዓለም ዓቀፍ ንግድ መተላለፊያም ነው። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የቆየው ጥላቻ ተወግዶ ሰላም መውረዱ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ብሎም  የምጣኔ ኃብት ትስስር  ለመፍጠር የሚያስችል ተስፋን እንደፈነጠቀ ታዛቢዎች ይናገራሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም