የጊኒዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ሊሰሩ ይገባል

54
ጋምቤላ ታህሳስ 6/2011 የጊኒ ዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ በጋምቤላ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 23ኛው ሀገር አቀፍ ዓመታዊ የጊኒ ዎርም በሽታ የማጥፋያ መረሃ ግብር አፈፃመም ግምገማ ተጠናቋል። የኢትዮጰያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ በዚህ ወቅት እንዳሉት የጊኒዎርም በሽታ ማጥፋት የሚቻለው የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ በሽታን ለማጥፋት ከአሁን በፊት በባለቤትነት መንፈስ በቅንጅት አብሮ ያለመስራት ችግሮች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማስቀረትና በሽታውን የማጥፋት መረሃ ግበርን ለማፋጠን ኢንስቲትዩቱ በመጠናቀቅ ላይ ካለው የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ እስከ ቀበሌ የሚዘልቅ ተቋማዊ አደረጃጀት ፈጥሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሽታውን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የውሃ ሴክተር ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በባለቤትነት ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ በካርተር ሴንተር የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ዘሪሁን ታደሰ በበኩላቸው "ባለፈው ዓመት በጋምቤላ ክልል የጊኒዎርም በሽታ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ 15 ሰዎች በበሽታው ተጠቅተው ነበር "ብለዋል። የችግሩን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት በተከናወኑት ስራዎች እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆች ዓመት በሽታው በሰው ላይ አለመከሰቱንና ይህም የተሻለ ውጤት የታየበት ዓመት እንደነበር ተናግረዋል። ሆኖም በሽታውን ለማጥፋት ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱን ጠቁመው ይህም በተለይም የመንግስት ባለድርሻ አካላት በሽታውን ለማጥፋት በባለቤትነትና በቁርጠኝነት ያለመስራት ችግር መሆኑን ጠቁመዋል። በሽታውን ለማጥፋት ባለድርሻ አካላት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተው ተጠሪው ካርተር ሴንተር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ የጊኒዎርም በሽታን ከጋምቤላ ክልል ብሎም ከሀገሪቱ ለማጥፋት የተሻሉ ስራዎች በመከናወናቸው በሽታው ቀንሶ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የክልሉ  ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክትር ኡማን አሙሉ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት  እንደገና አገረሽቶ እንደነበር አስታውሰው ለዚህም ምክንያቱ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ለሰራተኞቻቸው ንጹህ ውሃ ባለማቅረባቸው እንደሆነ ተናግረዋል። ባለሀብቶች ለሰራተኞቻቸው ንጹህ መጠጥ ውሃ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገዳጅ  ሁኔታ እንዲቀመጥ መደረጉን አስረድተዋል። በጋምቤላ ከተማ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የግምገማው መድረክ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመስራት በሽታን ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለማጥፋት መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡ በሽታው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአራት የአፍረካ ሀገራት በስተቀር በሌሎች የዓለም ሀገራት መጥፋቱን በመድረኩ ተገልጿል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም