በወረጃርሶ ወረዳ የጦር መሳሪያዎችና የኮንትሮባንድ እቃዎች ሲያዘዋውሩ የተገኙ 20 ግለሰቦች ተያዙ

70
ፍቼ ታህሳስ 6/2011 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በወረጃርሶ ወረዳ ጎሃ-ፂዮን ከተማ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችና የኮንትሮ ባንድ እቃዎች ለማዘዋወር ሲሞክሩ የተገኙ  20 ግለሰቦችን መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ የወረዳው ፖሊስ ከህዳር 25/2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአስር  ቀናት  ባካሄድው  ድንገተኛ ፍተሻ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን  በሁለት የቤት መኪናና  በሶስት የነዳጅ መጫኛ  ቦቴ ተሽካርካሪዎች ውስጥ መያዙ ተነግሯሏል፡፡ የጦር መሳሪያዎች  ከጎረቤት ሃገር ገብቶ በአማራ ክልል በኩል ወደ መሀል ሀገር ለማዘዋወር ታልሞ  እንደነበር በድርጊቱ ተጠርጥረው ከተያዙት ግለሰቦች የምርመራ ቃል መረዳት እንደታቻለ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር መንግስቱ ከተማ ለኢዜአ ገልጸዋል። የተያዙት የጦር መሳሪያዎች ሁለት ብሬል መትረየስ፣16 ክላሽኮቭ፣ 43 ኤስኬኤስ ጠመንጃና 3 ሚንቶቭ እንዲሁም 12 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች 200 ከሚደርሱ ተተኳሽ ጥይቶች ጋር መሆኑን  አስታውቀዋል። በተጨማሪም ከአንድ ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው 89 ካርቶን ሽቶና ልዩ ልዩ  ሲጋራዎች  በቁጥጥር ስር  እንደዋለ አዛዡ አስረድተዋል። ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን የሚፈጽሙት የህዝብ በዓላትንና ጨለማን ሽፋን በማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢንስፔክተር መንግስቱ እንዳመለከቱት ተጠርጣሪዎቹ ሳናውቅ በአደራ የተቀበልነው እቃ ነው ቢሉም የሚሰጡት መረጃ እርስ በእርሱ የሚጋጭ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ምርመራው በከፊል ተጠናቆ ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው። ከተያዙት ተጠርጣሪዎቹ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ግለሰቦችን ፖሊስ ክትትል እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የህግ ባለሙያ  አቶ ኢሳያስ ጥበቡ የትኛውንም የጦር መሳሪያ በብዛትም ሆነ በተናጥል ያለ ፍቃድ መያዝ፣ ማዘዋወር፣ መሸጠና መለወጥ ከገንዘብ ቅጣት እስከ 15 ዓመት እንደሚያስቀጣ በህግ መደንገጉን ገልጸዋል። እንዲሁም በህብረተሰብ ውስጥ የፀጥታና ያለመተማመን ስጋት እንዲሰፍን ምክንያት ሆኖ ከቀረበ ደግሞ  ቅጣቱ ሊከብድ እንደምችልም አስረድተዋል። ሌላው የአካባቢው ነዋሪ የኃይማኖት አባት ቀሲስ ኃይለማሪያመ ኪሮስ የጦር መሳሪያ ግጭትን የሚያባባስና ወደ አልተፈለገ ሁኔታ  የሚከት በመሆኑ ዜጎች ለሰላም፣ ለፍቅርና ለመቻቻል ቦታ በመስጠት ወንጀልን መከላከል እንዳለባቸው መክረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም