ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሀዘን መግለጫ አስተላለፉ

70
ታህሳስ 6/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለፁ። ኢትዮጵያን ለ12 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ያለገሉት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ትናንት ሌሊት በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ከ1994 እስከ 2006 ዓ.ም የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በማረፋቸው በኢፌዳሪ መንግሥት እና “በራሴ ስም የተሰማኝን ጥልቅ ኀዘን ለመግለጽ እወዳለሁ ብለዋል። ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የኢፌዲሪ መንግሥትን ለአስራ ሁለት ዓመታት ያህል በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ፣ በልዩ ልዩ ኃላፊነት ለሀገራቸው ረዥም ዘመን የሠሩ፣ በዕውቀታቸውና በሙያቸው ለሕዝባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰጡ፣ የታታሪነት፣ የቅንነትና፣ የሕዝባዊ አገልግሎት ሰጭነት ተምሳሌት እንደነበሩም ጠቅሰዋል። በፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ዕልፈት ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል። ታህሳስ 19 ቀን 1917 ዓ.ም አዲስ አበባ የተወለዱት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ፤ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ከፓርላማ አባልነት እስከ ፕሬዚዳንትነት አገራቸውን አገልግለዋል። ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ አፋርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ጣሊያንኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን የሚናገሩት አቶ ግርማ ከአንድ ዓመት በፊት በሞት ከተለዩአቸው ባለቤታቸው አምስት ልጆችን አፍርተዋል። መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚያስፈጽም ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን በቅርቡ አስፈላጊውን መግለጫ እንደሚሰጥም ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም