በልዩ ጣዕም የግብርና ምርቶች የንግድ ምልክትና ብራንድ ቢያገኙም ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ማህበራት ገለጹ

70
ደብረብርሃን ታህሳስ 5/2011 ባለ ልዩ ጣዕም የግብርና ምርቶችን በማዘጋጀት የንግድ ምልክት ቢያገኙም ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ በሰሜን ሸዋ ዞን የንግድ ምልክትና ብራንድ የተሰጣቸው ማህበራት ገለጹ፡፡ የዞኑ ህብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ማህበራቱ ተጠቃሚ ያልሆኑት በራሳቸው ችግር ነው ብሏል፡፡ የመንዝ በግ ልዩ ጣዕም ማህበር ሰብሳቢ አቶ አድማሱ ሰብስቤ ማህበሩ በ48 አባላት 1997 እንደተመሰረተ ጠቁመው በ2007ዓ.ም የንግድ ምልክትና ብራንድ እንደገኙ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በመስሪያ ቦታና የገበያ ትስስር በማጣት በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ  ገልጸዋል፡፡ የእንሰሳት ማቆያ መጋዝን እንዲሰጣቸውና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው የሚመለከተውን አካል ቢጠይቁም ምልሽ በማጣታቸው ሥራ ማቆማቸውን አመልክተዋል፡፡ የንግድ ምልክቱን ቢያገኙም በቂ የመስሪያ ቦታ ባለመመቻቸቱና የተፈጠረላቸው ገበያ ትስስር በመቋረጡ ተጠቃሚ መሆን አንዳልቻሉ የገለጹት ደግሞ የደብረሲና ቆሎ ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ዘውዲቱ በቀለ ናቸው፡፡ በ350 አባላት የሚመረተውን ልዩ ጣዕም ቆሎ ለደብርብርሃን ዩንቨርሲቲ ኪሎውን በ45 ብር ሲያስረክቡ ቢቆዩም ባልታወቀ ምክንያት በመቋረጡ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ "ለ15 ዓመት በግሌ ደብረሲና ከተማ አስፓልት ላይ ከሰራሁት ይልቅ በማህበሩ ተጠቃሚ መሆን ጀምሬ ነበርም"ብለዋል፡፡ በዞኑ ህብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት የሀገር ውስጥ ገበያ ትስስር ባለሙያ አቶ አታላይ ታከለ ተጠቃሚ ያልሆኑት በቦታና ገበያ ትስስር ችግር ሳይሆን በራሳቸው ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለሙያ እንዳሉት ችግራቸውም የተፈጠረላቸውን ገበያ ትስስርና የተሰጣቸውን ቦታ በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ነው፡፡ "ለሁሉም ማህበራት ከባለሃብቶች፣ ፋብሪካዎች፣ ሆቴሎችና ውጭ ሀገር ላኪዎች ጋር በተወሰነ ደረጃ የተፈጠረላቸውን ገበያ ትስስር በግልዊ ጥቅም፣ በምርት ጥራትና ብዛት ክፍተት ሊጠቀሙበት አልቻሉም" ብለዋል፡፡ የተለያዩ የንግድ ምልክት የተሰጣቸውም ምርቶች በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች በሚካሄዱ ባዛሮች ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ በማድረግ ተፈላጊነቱ ሲጨምርም በተደጋጋሚ የምርት እጥረት ማጋጠሙን የደብረሲና ቆሎ ማህበርን ጠቅሰው ጠቁመዋል፡፡ የመንዝ በግም ቢሆን ያላቸውን ትንሽ ቦታ ተጠቅመው ያረቧቸውን የሥጋ በጎች ከሀገር ውስጥና ውጭ ነጋዴዎች ጋር በገበያ ቢተሳሰሩም የሥጋው ጣዕም እንጂ ብዛት ስለሌለው ገበያው መዳከሙንም አንስተዋል፡፡ ሆኖም የቦታና የገበያ ትስስራቸውን ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋጋር እንዲፈታ  ማህበራት ብቻ ሳይሆን አምራች አርሶ አደሮችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ባለሙያው አመልክተዋል፡፡ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጥናት ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው ያሉ ችግሮችን በጥናትና ምርምር ምላሽ እንዲያገኙ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተፈጥሮ የነበረው የገበያ ትስስር ባለፈው ዓመት ወጪ ለመቆጠብ  ቢቋረጡም በተያዘው ዓመት ለማስቀጠል እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በዞኑ ለስድስት  የግብርና ምርቶች የንግድ ምልክትና ብራንድ መስጠቱ ተመልክቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም