ማህበሩ ከ13 ዩኒቨርሲቲዎች በአንስቴቲስት ሙያ በከፍተኛ ውጤት ለተመረቁ ተማሪዎች እውቅና ሰጠ

92
አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2011 የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ከሚገኙ 13 ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ በከፍተኛ ውጤት ለተመረቁ ተማሪዎች እውቅና ሰጥቷል። በተመሳሳይ ማህበሩ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የማደንዘዣ ህክምና ትምህርት መስራች ለሆኑትና ከኤርትራ ቆይታ ከ20 አመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ለመጡት ባለሙያ አቶ ከሰተ ተወልደብርሃን እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል። ማህበሩ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን 14ኛውን አመታዊ ጉባኤ "ርህራሄና ክብር፤ ጥንቃቄ የተሞላ የተቀናጀ የማደንዘዣ ህክምና ለመስጠት" በሚል መሪ ሃሳብ እያካሄደ ይገኛል። በዚህም ማህበሩ በኢትዮጵያ ከ13 ዩኒቨርሲቲዎች በማደንዘዣ ህክምና ዘርፍ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ለቆዩና በከፍተኛ ውጤት ለተመረቁ ተማሪዎች እውቅና ሰጥቷል። ተማሪዎቹ ዳግማዊ ምኒሊክ የህክምና ማዕከልን ጨምሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የዘርፉን ትምህርት ተከታትለው በከፍተኛ ውጤት ያጠናቀቁ ናቸው። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳሃርላ አብዱላሂ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር ከመንግስት ጎን በመቆም አገራዊ የጤና አገልግሎት ማስፋፋት፣ ጥራት መጠበቅና ጥሩ ስነ-ምግባር የተላበሱ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። የተሻለ ጥራት ያለው የቀዶ ህክምናና የማደንዘዣ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማድረስ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ድርሻ ጉልህ መሆኑንም ገልጸዋል። የዘርፉ ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት እየተፈጠረ ያለውን በቀዶ ህክምና የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን በመሙላትና ሙያውን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ረገድ ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ አንስቴቲስቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ልኡልአየሁ አካሉ በበኩላቸው፤ ማህበሩ በሙያው ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት፣  አዛኝ፣ ሩህሩህና ተገልጋይ አክባሪ ባለሙያ ለማፍራት እንደሚጥር ገልጸዋል። በማደንዘዣ ህክምና በትምህርታቸው ብልጫ ያሳዩ ተማሪዎች በሙያው ተግተው እንዲያገለግሉና እንዲበረታቱ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ሰዎች የማደንዘዣ ህክምና ላይ ያላቸው አመለካከት አናሳ እንደሆነ ጠቁመዋል። ሙያው በርካታ ሙያተኞች የሚፈሩበትና ደረጃውን የጠበቀ የማደንዘዣ አገልግሎት ለመስጠት ከሚያስችሉ መሳሪያዎችና መድሃኒቶች ጋር እየታገዘ የሚሰጥ በመሆኑ ከደህንነት ጋር በተያያዘ ሙያተኞች ስጋት እንዳይኖርባቸው አሳስበዋል። በጉባኤው ከ400 በላይ የአገር ውስጥና ከውጭ አገሮች የመጡ የማደንዘዣ ህክምና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም