የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚያጋጥማቸው ችግር ጥቆማ የሚሰጡበት ስርዓት ተዘረጋ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚያጋጥማቸው ችግር ጥቆማ የሚሰጡበት ስርዓት ተዘረጋ
65
አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2011 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በስልክ ጥቆማ የሚያደርጉበት ስርዓት መዘርጋቱን የአስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አስታወቀ። ሴክሬታሪያቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ኅብረተሰቡ ጥቆማ የሚሰጥባቸው የስልክ መስመሮች ይፋ ተደርገዋል። የሴክሬታሪያቱ ኃላፊ ወይዘሪት ፌቨን ተሾመ እንደተናገሩት፤ ኅብረተሰቡ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚገጥመውን ችግር ለአስተዳደሩ የሚያሳውቅበት ስርዓት ተዘርግቷል። አስተዳደሩ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከማቹ ችግሮችን መፍታት፣ ህጋዊነትን ማስፈን፣ የህግ የበላይነትን ማስከበርና ፍትህን ማረጋጥ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በተለይም መሬት ይዞታ ላይ ያለ አግባብ ታጥሮ የተቀመጠ ከ5 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ መግባቱን ጠቅሰው ለማህበረሰብ አገልግሎት፣ አረንጓዴ መናፈሻዎችን በማዘጋጀት ህዝቡ እንዲጠቀምበት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በተመሳሳይ በመዲናዋ በአምስት ክፍለ ከተሞች በህገ-ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 2 ሺህ የቀበሌ ቤቶች ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞችና በከፋ ድህነት ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች መተላለፉን አመልክተዋል። እንደ ወይዘሪት ፌቨን ገለጻ፤ በጎዳና ላይ በህገ ወጥ መንገድ ሲነግዱ የነበሩ ወጣቶች የመሸጫ ቦታ ወስደው እንዲሰሩ ተደርጓል። ''የከተማ አስተዳደሩን ካቢኔ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ እንደ አዲስ የማደራጀት ስራ ተከናውኗል'' ያሉት ኃላፊዋ አሁንም አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት መኖሩ በግምገማ መረጋገጡን ገልጸዋል። ባለጉዳይ ማመላለስ፣ ጉዳዮችን ቶሎ አይቶ መልስ ያለመስጠት፣ በስራ ሰዓት ስብሰባ ማካሄድ እና መሰል ችግሮች አሁንም እንደሚስተዋሉ የገለጹት ወይዘሪት ፌቨን ''ለውጥ እንደሌለ በማስመሰል ህዝቡ እንዲማረር ሆን ብለው የሚሰሩ አካላት መኖራቸው ተረጋግጧል'' ብለዋል። ወይዘሪት ፌቨን እንዳሉት፤ የከተማ አስተዳደሩ ህዝቡን ለማማረር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል። ከእርምጃው ጎን ለጎን ኅብረተሰቡ የሚገጥሙትን አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለከንቲባ ጽህፈት ቤት በስልክ ጥቆማ እንዲያቀርብ ወይዘሪት ፌቨን ጥሪ አቅርበዋል። ''በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ ዳር እንዲደርስ ኅብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ኃላፊቱን ሊወጣ ይገባል'' ያሉት ኃላፊዋ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አስተዳደሩ መዋቅሩን በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራ በጥናት ላይ ተመስርቶ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ብልሹና ኢፍትሃዊ አሰራር ሲያጋጥማቸው በሚከተሉት የስልክ ቁጥሮች ጥቆማ እንዲያቀርቡ ተጠይቋል። አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 011 8 54 84 23 አራዳ ክፍለ ከተማ 011 8 54 83 97 አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 011 8 54 82 57 ቦሌ ክፍለ ከተማ 011 8 54 84 15 ጉለሌ ክፍለ ከተማ 011 8 54 86 38 ቂርቆስ ክፍለ ከተማ 011 8 54 97 53 ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 011 8 54 78 96 ልደታ ክፍለ ከተማ 011 8 54 97 07 ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 011 8 54 80 67 የካ ክፍለ ከተማ 011 8 54 82 52