ፍርድ ቤቱ በብርጋዴር ጀኔራል ጠና ቁርንዲ መዝገብ በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

1589

አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በብርጋዴር ጀኔራል ጠና ቁርንዲ መዝገብ በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ 25 የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ ስራ ኃላፊዎች ላይ ከ10 እስከ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

በመዝገቡ የተካተቱ ተጠርጣሪ ሌተናል ኮሎኔል ዙፋን በርሄ በ50 ሺህ ብር ዋስትና እንዲወጡ የፈቀደ ሲሆን ከአገር እንዳይወጡ የመታወቂያና የፓስፖርት ቅጂ ለኢምግሬሽንና ስደተኞች ጉዳይ እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ ላይ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ አካሂዶ 10 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ሰባት ተጠርጣሪዎች ታህሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም፤ 14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው 18 ተጠርጣሪዎች ታህሳስ 18 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል።

በተያያዘ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር በተያያዘ በሙስና የተጠረጠሩ ትዕግስት ታደሰ፣ ፍጹም የሺጥላና ቸርነት ዳና ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ቢሆንም መደበኛ የችሎት ሰዓት በማለቁ ለሰኞ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።