አይ .ኤፍ .ሲ የጥቃቅንና አነስተኛ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞችን በገንዘብ የመደገፍ ፍላጎት አለው

199
አዲስ አበባ ታህሳስ 5/2011 የጥቃቅንና አነስተኛ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞችን በገንዘብ የመደገፍ ፍላጎት እንዳለው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር(አይ ኤፍ ሲ) አስታወቀ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፊሊፕ ሎሀውሩን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር (አይ ኤፍ ሲ) የዓለም ባንክ አንዱ ክንፍ ሲሆን የግሉን ዘርፍ በፋይናንስ የሚረዳ ድርጅት ነው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ከውይይቱ በኋላ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ የጥቃቅንና አነስተኛ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞችን ለማብዛት የአይ ኤፍ ሲ ድጋፍ አስፈላጊ ነው። ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር ባንኮችን የሚደግፍ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ከዚህ ቀደም ባንኮች ለብድር ይጠይቁ የነበረውን ማስያዣ በማስቀረት ባንኮች ለጥቃቅንና አነስተኛ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞች ለማበደር የሚችሉበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹም ገልጸዋል። አገሪቱ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የሥራ እድል ፈጠራን ለመተግበር እንቅስቃሴ ላይ የምትገኝ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በቀጣይ ተከታታይ ምክክር በማድረግ ወደ ሥራ እንደሚገባ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን ተናግረዋል። የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፊሊፕ ሎሀውሩን በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው በግሉ ዘርፍ እንደመስራቱ መጠን የጥቃቅንና አነስተኛ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዞችን የመደገፍ ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል። አይኤፍሲ የአለም ባንክ ቡድን አባል ሲሆን በማደድግ ላይ ባሉ አገሮች የግል ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ዓለም ዓቀፍ የልማት አጋር ነው። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ከድህነት እንዲወጡና ኑሯቸው እንዲሻሻል የገንዘብና አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን የሚያቀርብ ተቋም ነው። ከዚህ ባለፈም በስራ ዕድል ፈጠራና በሌሎች የቢዝነስ መስኮ የምክር አገልግሎት ይሰጣል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም