ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራ ገለጸች

1595

ሀዋሳ ታህሳስ 5/2011 ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላትን ረጅም ዓመታት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት በማጠናከር በድንበሮቻቸው አካባቢ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር እንደምትሰራ ሰላም ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ መካኒዝም ድንበር ተሻጋሪ የሰላም ጉባኤውን ዛሬ በሀዋሳ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

ጉባኤው ሲጀመር የሰላም ሚኒስትር ዴኤታው  አቶ ዘይኑ ጀማል እንዳሉት ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ዘመናት  የቆየ ታሪካዊና ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት አላቸው፡፡

ሁለቱ ሀገራት በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በዕምነትና በኑሮ ዘይቤያቸው ተመሳሳይነት ያላቸውና አንዱ የአንዱን ድንበር በመሻገር በሰላም አብረው የሚኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ ባለበት ሁኔታ በሁለቱ ሀገራት  በሞያሌ፣  በደቡብ ኦሞ፤ ቱርካና አዋሳኝ አካባቢዎች ከድርቅ ድህነት፤ በግጦሽና ውሀ ምክንያት አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች መስተዋላቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይህን ግጭት ለመፍታት በነዚህ አካባቢዎች በማህበረሰብ ደረጃ የሰላም ውይይት ተደርጎ ውሳኔዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ የሚታየውን ግጭት ለማስቆም የሚያስችል የመፍትሄ አቅጣጫ ጉባኤው ያስቀምጣል ብለው እንደሚጠብቁም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

ታሪካዊ ግንኙነታቸው ተጠናክሮ በሁለቱ ሀገራት መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ኢትዮጵያ እንደምትሰራ አመልክተዋል፡፡

የኬንያ የሀገርው ውስጥ ሚንስቴር ተወካይ ሚስተር ፒተር ታሁኩ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ኬንያ ጠንካራ መሰረት ላይ የተጣለ የረጅም ጊዜ ሰላማዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በጆሞ ኬንያታ ዘመን ከአጼ ኃይለስላሴ ጋር የተመሰረተው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በአሁኑ ወቅትም በኡሁሩ ኬንያታና በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ መካከል ያለውም በሰላም፣ ኢኮኖሚና በሌሎች መስኮች ላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

ተደጋጋሚ ድርቅ፣ የውሀ እጥረትና የተፈጥሮ ሀብት መመናመን በአካባቢው ለግጭት ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ግጭቱን  በመፍታት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት ለማስቀጠል የኬንያ መንግስት ተኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ መካኒዝም ሚስተር ካምሉስ ኦሞጎ እንዳሉት በዚህ ጉባኤ ሁለቱ ሀገራት በሞያሌና በደቡብ ኦሞ፤ ቱርካና አካባቢዎች ያለውን ግጭት ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነው፡፡

በታችኛው ማህበረሰብ ደረጃ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በተደረጉ ውይይቶች የችግሮቹን ምንጮች ተለይቶ ለችግሩ መፍትሄ የሚሆን አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

የዛሬው በከፍተኛ ኃላፊዎች ደረጃ በሚካሄደው ጉባኤ በማህበረሰብ ደረጃ በተደረገው ውይይት የተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ በመምከር ውሳኔ ላይ እንደሚደረስ የሚጠበቅ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የሀዋሳ ጉባኤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር የሚያስችል ውሳኔ ይጠበቃል፡፡

በጉባኤው የኦሮሚያ፣ ደቡብና የሶማሌ ክልል፤ የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች በኬንያ በኩል ደግሞ የመርሳቤት የቱርካናና ሞያሌ አካባቢ ገዥዎች እየተሳተፉ ነው፡፡