በሞያሌ ከተማ በተከሰተ ግጭት 21 ሰዎች ሲሞቱ 61 ቆስለዋል

142
ጅግጅጋ ታህሳስ 5/2011 በሞያሌ ከተማ በተከሰተ ግጭት 21 ሰዎች መሞታቸውንና 61 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን የሶማሌ ክልል  መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ  ገለጸ። በሞያሌ ከተማና አከባቢዋ የሚከሰቱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ውይይት እየተደረገ ነው። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሱረው መሐመድ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት በዜጎች ላይ ጉዳቱ የደረሰው ባለፉት ሁለት ቀናት በደረሱ ግጭቶች ነው። በግጭቱ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ወገኖችን ለመርዳት ሁለት ቡድኖች ወደ አካባቢው ተልከው ሕክምና መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል። በግጭቱ ከተፈናቀሉት ወገኖች የተወሰኑት ወደ ኬንያ መሰደዳቸውንም አቶ መሐመድ ተናግረዋል። በመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች ደግሞ የክልሉ መንግሥት እርዳታ ለማቅረብ እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል። በሞያሌ ከተማና አከባቢዋ የሚከሰቱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የፌዴራል፣የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችና ባህላዊ መሪዎች እየተወያዩ መሆናቸውን ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት በሞያሌ ከተማና አካባቢውና የሚታዩ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል። ሕዝቡ የሁለቱ ክልሎችን ሕዝብ ወደ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ለማስገባት የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንቅስቃሴ ለማክሸፍ እንዲረባረብ አቶ መሐመድ ጠይቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም