የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመጪው ሚያዚያው ወር ወደ ልማት ስራ ይገባል

140
ባህርዳር ታህሳስ 5/2011 የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በመጪው ሚያዚያው ወር ተጠናቆ ወደ ልማት ስራ እንደሚገባ የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡ ከግንባታው በተጓዳኝ አልሚ ባለሃብቶችን ወደ ፓርኩ የማስገባት ስራ እየተከናወነም ተመልክቷል። የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኛቸው አስረስ ለኢዜአ እንደገለጹት በዲዛይን መለዋወጥ ዘግይቶ ግንባታው የተጀመረው የፓርኩ የመጀመሪያው ምዕራፍ አሁን ላይ ግማሹ ተጠናቋል። በዚሁ ምዕራፍ በሚለማው 260 ሄክታር መሬት ውስጥ የ12 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ እንዲሁም የማፋሰሻ፣ ውሃ ፣ ስልክና የኤሊክትሪክ መብራት መስመሮች ዝርጋታ እየተከናወነ ነው። የአምስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ መጠናቀቁንና የሦስት ማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ያመለከቱት ስራስኪያጁ የአስተዳደርን ጨምሮ የ11 ትላልቅ ህንፃዎች ግንባታም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተጨማሪም የ9 ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር የአጥር ስራ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ በ231 ሚሊዮን ብር ወጪም የሞዴል ሸድ ግንባታ መጀመሩን ገልጸዋል። ስራስኪያጁ እንዳሉት  እስካሁን ለተካሄደው የመሰረተ ልማት አውታር ዝርጋታና የህንፃ ግንባታዎች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ ለፓርኩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ማስፈጸሚያ እስከ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል። በተለያዩ ተራጮች እየተከናወነ ባለው የህንፃና  የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከአምስት ሺህ ለማያንሱ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል። የመጀመሪያው ምዕራፍ የፓርኩ ግንባታ በመጪው ሚያዚያ ወር መጨረሻ  ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ልማት ስራ እንደሚገባ ስራ አስኪያጁ አስታወቀዋል፡፡ ለፓርኩ ግብዓት የሚሆን የምርት መሰብሰቢያ በምዕራብና ምስራቅ ጎጃም እንዲሁም በአዊ ዞን በተመረጡ ወረዳዎች 7 ማዕካላትን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው የሞጣ ማዕከል ግንባታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከፓርኩ ግንባታ በተጓዳኝም በፓርኩ ውስጥ ማልማት የሚችሉ አቅም ያላቸው የሃገር ውስጥና የውጭ  ባለሃብቶችን የማግባበት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል። እስካሁንም ኢትዮጵያውያንና ቻይናውያን ጥምርት የተቋቋመው የዘይት፣ የስታርችና የእንስሳት መኖ ማልማት የሚችል ድርጅት በሁለት ቢሊዮን ሰባት መቶ ሚሊዮን  ብር ካፒታል ለማልማት ወደ ፓርኩ ገብቶ በተመቻቸለት 12 ሄክታር መሬት ግንባታ መጀመሩን ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል። ሌሎች በወይንና ሌሎች የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች መሰማራት የፈለጉ ብዛት ያላቸው ባለሃብቶች ጥያቄ ማቅረባቸውንም ጠቅሰዋል። የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የብዕር እህል፣ የጥራጥሬ፣ የሰሊጥ፣ የአትክልትና ቅጠላቅጠል፣ የማርና ሰም፣ ወተትና የስጋ ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ቅድሚያ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በፓርኩ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከልም ወጣት አድምጠው ስጋቴ በሰጠው አስተያየት የፓርኩ መምጣት መተዳደሪያ የሚሆን የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ የአናጺነት ሙያ መቅሰሙን ተናግሯል። ከፓርኩ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ  በአካባቢውም የተሻለ እድገት እንዲመዘገብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ገልጿል፡፡ "የቤተሰቤ  የእርሻ መሬት ለፓርኩ በመከለሉ ምክንያት ቅድሚያ ተሰጥቶን የስራ እድል ተፈጥሮልን የተሻለ ገቢ ማግኘት በመቻሌ ተጠቃሚ ሆኛለሁ"  ያለችው ደግሞ ወጣት ውዴ ተስፋሁን ናት። የአስረኛ ክፍል ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ወደ ስራ እንደተሰማራች ያመለከተችው ወጣቷ በቀጣይም በሚገነቡት ፋብሪካዎች በተለያየ መስክ በመስራት የበለጠ ተጠቃሚ እሆናለሁ ብላ እንደምትጠብቅም  ተናግራለች። የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሁለተኛና ሦስተኛ ዙር ግንባታም በቀጣይ እንደሚጀመር ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም