''ከለውጡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል''-- ሴት የሰላም አምባሳደሮች

101
አሶሳ ታህሳስ 5/2011 በአገሪቱ በተጀመረው ለውጥ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን አመራሩ ሰላምን ለማረጋገጥ መሥራት እንደሚገባው ሴት የሰላም አምባሳደሮች ገለጹ። ቡድኑ ከክልሉ ኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡ ቡድኑ ከዘጠኙ ክልሎች፣ ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች የተውጣጡት እናቶች በአገሪቱ ሠላም የማስፈን ዓላማ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዘ ክልል አሶሳ ከተማ ተገኝተው ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰንና የካቢኔ አባላት ጋር ትናንት ተወያይተዋል፡፡ የክልሉ አመራሮች ለሰላም መስፈንና የሕዝቡን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። ቡድኑ በዚሁ ወቅት አሶሳና አካባቢው ያልተረጋጋ እንዳልሆነ ቢነገረውም፤ ለያዙት ዓላማ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅቶ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በቆይታቸው ከአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ባደረጓቸው ወይይቶች እንደ ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች እንደገጠማቸው ሁሉ የክልሉ አመራሮች ሕዝብን በማገልገል ረገድ ችግሮች እንዳለባቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ኢትዮጵያዊነትን የማይገልጹ የጸጥታ ችግሮች የኅብረተሰቡን ሠላም በማወክ ላይ በመሆናቸው አመራሮቹ ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት ዜጎች ከስጋት የተላቀቀ ሕይወት እንዲመሩ ማድረግ ይገባችኋል ብለዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩና ካቢኔአቸው ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናቶቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በሌሎች ክልሎች ባስተላለፉት የሠላም መልዕክት ስኬታማ መሆናቸው የተናገሩት እነዚሁ የሠላም መልዕክተኛ እናቶች፣ አመራሮቹ መልዕክታቸውን እንደሚተገብሩት እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በበኩላቸው የሠላም አስፈላጊነት የማያጠያይቅ መሆኑን አመልክተው፣በተለይ ለህጻናትና ሴቶች የሰላም እጦት ዋነኛ ተጠቂዎች መሆናቸውንም አመልክተዋል። ሴት የሰላም አምባሳደሮች እያከናወኑት ላለው ተግባር አድናቆታቸውን ገልጸዋል። የቡድኑ ወደ ክልሉ መምጣት ሠላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት አቅም እንደሚፈጥር አስታውቀዋል፡፡ አመራሩ ኃላፊነቱን በአግባቡ ከተወጣ ሰላምን ማስጠበቅ ይቻላል በሚለው ሃሳብ በመስማማት ጥሪያቸው ተቀብለው የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ ቃል ገብተዋል፡፡ የሴት የሰላም አምባሳደሮች ቡድን በቀጣይ ወደ ጋምቤላ ክልል ይጓዛል። ቡድኑ እስካሁን ዘጠኝ ክልሎችን ጎብኝቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም