በቱሪስቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን የሚያቃልሉ እርምጃዎች ይወሰዳሉ -የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

106
አዳማ ታህሳስ 5/2011 በኢትዮጵያ ቱሪስቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች የሚያቃልሉ እርምጃዎች ለመውሰድ እየተዘጋጀ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። ወከባ ፣ ዘረፋ ፣ ማጭበርበርና ስርቆት ቱሪስቶቹ የሚገጥሟቸው ዋነኛ ችግሮች ሆነው ተቀምጠዋል። ሚኒስቴሩ በጎብኚዎች ላይ የሚያጋጥሙ የፀጥታና ደህንነት ስጋቶችን ለይቶ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ያካሄደውን የጥናት ግኝት ትናንት በአዳማ ከተማ ለውይይት ቀርቧል ። ለሁለት ቀናት የሚቆየው መድረክ ” የቱሪስት ደህንነት ማረጋገጥ ለቱሪዝም አድገት የሚኖረው ፋይዳ ”በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ነው ። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር መድረኩን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ቱሪዝም የኢኮኖሚውን ዘርፍ ለመደገፍ ባለው ፋይዳ ቱሪስቶች የሚያጋጥሟቸን ችግሮች በተቀናጀ መልኩ ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ነው። ዘርፉን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ሰላም  የጀርባ አጥንት ብቻ ሳይሆን፤ የቱሪዝም  ህይወት የሚንቀሳቀስበት ልብ ነው ብለዋል ። የአገሪቱን የቱሪስት መዳረሻዎች የተለያዩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በርካታ ሕገወጥ ተግባራት እንደሚያጋጥሙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል ። ወከባ ፣ ዝርፊያ ፣ ማታለልና መሰል ወንጀሎች በብዛት እንደሚታዩ የገለፁት ወይዘሮ ቡዜና፣ ሕገ ወጥ አስጎብኚዎች በሚፈፅሙት ተገቢ ያልሆነ ተግባር የአገሪቱ መልካም ገፅታ እየተበላሸ ነው ብለዋል። በአገርና በዓለም ያሉትን ወቅታዊ ሁኔታዎችንና ተጨባጭ ተሞክሮዎችን በማጥናት የማስተካከያ  እርምጃ እንደሚወሰድ አስረድተዋል ። በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የጥናትና ማማከር ባለሙያ ኢንስፔክተር ዳምጤ ውዱ ባቀረቡት ጥናት በቱሪስቶች ላይ ዝርፊያ፣ድብደባ ፣ ማጭበርበር፣ አስገድዶ መድፈር፣ አስፈራርቶ ገንዘብ መቀበልና እስከ ግድያ የሚደርስ የጥቃት ወንጀል የሚፈፀምበት አጋጣሚ መኖሩን ተናግረዋል። አልፎ አልፎ የሚስተዋሉት ግጭቶችም የጎብኚዎችን ምቾት በመንፈግ አሉታዊ ተፅእኖ በማሳደር ላይ መሆናቸው ተመልክቷል። ልመናም አንዱ ቱሪስቶችን ከሚያዋከቡ ድርጊቶች መካከል የሚጠቀስና የጎብኚዎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የማስተካከያ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚያስፈልግ በጥናቱ ተጠቁማል። አብዛኛዎቹ ስጋቶችና ጥቃቶች በአስጎብኚዎች፣በባለሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች ፣ በሽፍቶችና  በሥነ ሥርዓት አስከባሪዎች እንደሚፈጸሙ ያመለከቱት ኢንስፔክተር ዳምጤ፣በድርጊታቸው ተይዘው በሕግ የተቀጡ መኖራቸውን አስረድተዋል ። ሁሉንም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ባሳተፈው የምክክር መድረክ ከሚመካከርባቸው ጉዳዮች የቱሪዝም ዕድገት ለሰላም መስፈን፣ የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ፋይዳና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ለቱሪስት ፖሊሲ መቋቋም የሚረዱ ተግባራትን በመለየት አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷንና ዘንድሮም ገቢውን ወደ 5ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የጎብኚዎች ቁጥርም አምና ከነበረው 934 ሺህ 923 ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል። በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጨረሻ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር፣ የጎብኚዎች ቁጥር ደግሞ ወደ ሁለት ሚሊዮን ለማሳደግ ታቅዷል። ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አምስት ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ አገሮች አንዷ የማድረግ ግብ ተይዞ እየተሰራም ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም