ለጋምቤላ ሆስፒታል አገልገሎት ጥራት መጠበቅ ድጋፋችንን እናጠናክራለን---ዶክተር አሚር አማን

87
ጋምቤላ ታህሳስ 5/2011 የጋምቤላ ሆስፒታል ጥራቱን የጠበቀ  የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ለሚያደርገው ጥረት መሳካት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን አስታወቁ፡፡ ሚኒሰትሩ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ሆስፒታሉንና በአካባቢው የሚገኘውን የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲን ጎብኝተዋል፡፡ በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ሆስፒታሉ ለህብረተሰቡ የተሻለ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች ነው፡፡ ሆስፒታሉ በተለይም ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ከህክምና አገልግሎት ተጠቃሚው ህብረተሰብ ይነሱ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በኩል ያሳየውን ለውጥ በሌሎች ዘርፎች  መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ሚኒስቴሩ  ሆስፒታሉ ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ለሚያደርገው  ጥረት መሳካት የህክምና መሳሪዎችና ቀደም ሲል ሲሰጣቸው የቆዩት ሌሎች ድጋፎችንም  እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪ  በክልሉ የሚገኘውን የፌዴራል የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የመድኃኒት መደብሩን የውስጥ አደረጃጀቱን ለማሻሻል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም አመልክተዋል፡፡ የጋምቤላ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኡማን አሙሉ በበኩላቸው "የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በክልሉ የተሻለ የህክምና አገልግሎት እንዲኖር ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል "ብለዋል ። በተለይም በሆስፒታሉ ውስጥ የጎደሉ የህክምና መሳሪያዎችን ለማሟላትና ሌሎች ችግሮችን ለማቃለል ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን ገልጸዋል፡፡ የቢሮው ኃላፊ እንዳሉት በሚሰጠውም ድጋፍ በሆስፒታሉ ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ሚኒስትሩ ከጉብኝታቸው በተጨማሪ ከሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም