የጋሞ ማህበረሰብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በዩኔስኮ መመዘገብ አለበት-የጋሞ ዞን ምክር ቤት አባላት

1627

አርባምንጭ ታህሳስ 5/2011 የጋሞ ማህበረሰብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምሀርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ)መመዝገብ እንዳለበት የጋሞ ዞን ምክር ቤት አባላት አስታወቁ፡፡

ባህሉ ሴቶች ነጠላቸውን በማንጠፍ ሰላም እንዲወርድ የሚያደርግ ነው።

አባላቱ ከኢዜአጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት የማህበረሰቡ መለያ የሆነውን የግጭት አፈታት ባህል በዓለም ደረጃ ለማስተዋወቅ ምዝገባው መከናወን ይኖርበታል።

ባህሉ ለልማት፣ለሰላም፣ለመልካም አስተዳደርና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ባለው ፋይዳ ምዝገባውን ማካሄድ አስፈላጊነት ያስረዳሉ፡፡

የምክር ቤቱ አባል አቶ ሻምበል ሻኜ ማህበረሰቡ ከአያት ቅድመ አያት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ ያመጣውን ግጭቶች ሲከሰቱ አባቶች ርጥብ ሣር ይዘው የሚፈቱበት ሥርዓት ዕውቅና እንዲያገኝ መሥራት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።

ባህሉ ከአጼዎቹ ሥርዓት ጀምሮ በዳራማሎ፣በቦንኬ፣ በጨንቻና በሌሎች የዞኑ አካባቢዎች ግጭቶች ሲከሰቱ  ባህላዊ ሥርዓቱን ተከትሎ ሲካሄድ መቆየቱን  ተናግረዋል፡፡

ባህሉን ተላልፎ ጥፋት መፈጸም በማህበረሰቡ ዘንድ ”ጎሜ” ወይም የሚያስቀስፍ ነው ተብሎ ስለሚታመንና ጥፋት ፈጻሚው በሕዝቡ እንዲገለል ስለሚያደርግ ግጭቱ ወደ ከፋ ደረጃ ሳይደርስ እንደሚፈታበትም አስታውቀዋል፡፡

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ጣሰዉ ጨቾ በበኩላቸው ባህሉ በአባቶች ብቻ ሳይሆን፤እናቶችም ግጭት ሲከሰት ነጠላቸውን መሬት ላይ በማንጠፍ እንደሚያወግዙና ግጭቱም ወዲያዉኑ እንደሚያስቆሙ ተናግረዋል።

ባህሉ የሕዝቡን ሰላም ከመጠበቅም በላይ ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓትን በማገዝ ሚናው ጉልህ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡

ዘመን ተሻጋሪዉ የእርቅ ሽምግልና ባህል ቢመዘገብ ለትውልድ ጠቀሜታው እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

ምክር ቤቱ የአያትና ቅድመ አያቶችን ባህል ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ኢሳያስ እንድርያስ በበኩላቸው ከግለሰብ ጀምሮ ግጭቶችን ሲፈቱበት የቆየው ባህል በድርጅቱ መመዝገብ እንደሚገባው ይናገራሉ።

የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አርኮ ደምሴ ሰላም ለሰው ልጆች ያለውን ጥቅም በመረዳትና ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ በድርጅቱ ለማስመዝገብ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቱ ዙሪያ በጥናት ሊያዳብሩት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የጋሞ ማህበረሰብ ባህላዊ የእርቅ ሥርዓት ዕውቅና ያገኘው በዚህ ዓመት መግቢያ ላይ በቡራዩ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የዓርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶችን በማረጋጋት የጋሞ አባቶች በተጫወቱት ሚና  እንደነበር ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አባቶቹ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለአባቶቹ የሰላም ዋንጫ ማበርከታቸዉ ይታወሳል፡፡