ከነጦር መሳሪያቸው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለመግባት ከሞከሩት የሠራዊት አባላት መካከል 66ቱ ተቀጡ

105
አዲስ አበባ  ታህሳስ 4/2011 ከወራት በፊት ከነ ጦር መሳሪያቸው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለመግባት ሙከራ አድርገው ከነበሩት የመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል በ66ቱ ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ። ባለፈው መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም የተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከነ ጦር መሳሪያቸው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለመግባት ሙከራ አደርገው እንደነበር ይታወሳል። ከእነዚህ መካከል በ66ቱ ላይ በቀዳማይ ወታደራዊ ፍርድ ቤት አማካኝነት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል። የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ዘውዱ በላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ ከነ ጦር መሳሪያቸው ወደጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለመግባት ያደረጉት ሙከራ የሠራዊቱን ክብር የሚቀንስ በመሆኑ የቅጣተ እርምጃው ተወስዷል። ''ማንኛውም ኃይል ወደ ቤተ መንግስት የሚገባው በምርጫ ብቻ እንጂ በጦር መሳሪያ በማስገደድ መሆን የለበትም ብሎ የሚታገል ሠራዊት ነው ያለው'' ብለዋል። ወታደራዊ ፍርድ የተላለፈባቸው የሠራዊቱ አባላት የፈጸሙት ተግባር የመከላከያ ሠራዊት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያገኘውን ክብር የሚቀንስ እንደሆነም ነው ሜጀር ጀነራል ዘውዱ ያብራሩት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም