በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ

94
አሶሳ ታህሳስ 4/2011 በአገሪቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ሲጥሱ የነበሩ ግለሰቦች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ አንዳንድ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎቹ እንዳስታወቁት የዜጎችን ሰብዓዊ መብትና ክብር በመጣስ ሰብዓዊ መብቶች እንዲጓደሉ ያደረጉ አካላት በሕግ ሊዳኙ ይገባል። ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተላለፈው በኢትዮጵያውያን የተፈጸመውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያሳየውን ዘጋቢ ፊልም ዘግናኝ ሆኖ እንዳገኙትም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። አቶ አብዱ ሰይድ የተባሉ ነዋሪ እንደሚሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በየትኛውም የኢትዮጵያ መንግስታት ከተፈጸሙ ወንጀሎች የከፋና ድርጊቱን የፈጸሙት ኢትዮጵያዊ ስብዕና ያላቸው አይደሉም፡፡ “የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በተፈጸመበት ወቅት የነበረው መንግሥት አገሪቱን አየመራ ነበር” ለማለት እቸገራለሁ የሚሉት አስተያየት ሰጪው “የተቀረጹ ህጎች ተግባራዊ ባለመደረጋቸው ግለሰቦች በህዝብና በአገር ላይ ጫፍ የረገጠ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጽሙ አስችሏቸዋል” ይላሉ፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለዜጎች አገር ጥሎ መሰደድ ዋነኛ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚሉት አቶ አብዱ፣''የመንግሥት የደህንነት መዋቅር ዜጎችን ከመጠበቅ ይልቅ ሲያሸብር እንደነበር ማሳያ ነው'' ብለዋል፡፡ ድርጊቱን የፈጸሙ ግለሰቦች ከየትኛውም የዓለም ክፍል በአስቸኳይ ተይዘው ለፍርድ ሊቀርቡ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ “ወንጀል ግለሰባዊ ወይም ቡድናዊ እንጂ፤ ህዝባዊ አይደለም” የሚሉት አስተያየት ሰጪው “የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን ከየትኛውም ብሄር ለማያያዝ የሚሞክሩ ግለሰቦች ካሉ ለውጡን አደናቃፊና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንደሚጋጩ ሊረዱ ይገባል” በማለትም ተናግረዋል፡፡ በወንጀሉ የሚጠየቁ ግለሰቦች ከፈጸሙት ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተመሳሳይ እርምጃ ይወሰድባቸው የሚል እምነት የለኝም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ድርጊቱን በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ የሚሰጠው ፍትህ አሁን ላለው የለውጥ አመራር ትምህርት በሚሰጥ መልኩ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አቶ አብዱ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ዩሃንስ ያለው የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው መንግሥት በአገሪቱ የሠራቸው በርካታ በጎ ነገሮች ቢኖሩም፤ ድርጊቱ አገርን የካዱና በዜጎች ላይ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች በውስጡ አቅፎ መቆየቱን እንደሚያሳይ ይገልጻሉ፡፡ ማንም ወንጀል ሰርቶ መደበቅ አይችልም የሚሉት ነዋሪው “የጊዜ ጉዳይ እንጂ፤ ተሸፋፍኖ የሚቀር ነገር እንደሌለ ዶኩሜንተሪ ፊልሙ አሳይቶአል” ብለዋል፡፡ ''አሁን ያለው የለውጥ አመራር ከዚህ ስህተት ይማራል እንጂ አይደግምም” የሚል እምነት ያላቸው አቶ ዮሐንስ፣ “የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን ለማስቀጠል የዜጎችን ሃብት ዘርፈው መልሰው ዜጎችን ለማጋጨት የሚጠቀሙ አሉ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ኅብረተሰቡ አገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚጥሩ ኃይሎች ከለውጥ አመራሩ ጎን በመቆም አጥብቆ ሊታገል እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡ ዘጋቢ ፊልሙን እያነቡ መከታላቸውን የሚናገሩት ደግሞ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ምንታምር አበበ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡ “ወንጀሉን የፈጸሙት የማያዳግም ቅጣት ያስፈልጋቸዋል” የሚሉት ነዋሪዋ፣''ይህም አንዳችን ሌላችንን እየተበቃቀልን ለትውልድ ጭካኔን በምናወርስበት መንገድ መሆን የለበትም” ሲሉ መክረዋል፡፡ በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት የተጻፈውና የተገበረው ለየቅል እንደሆነ  የተናገሩት አስተያየት ሰጪዋ፣  አሁን ያለው የለውጥ አመራር በዋናነት የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከርና ሕግ በማስከበር ላይ መሥራት እንደሚጠበቃቸው አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም