ለስንዴ ምርታቸው ተገቢውን የገበያ ዋጋ ማጣታቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ

76
ጎባ ታህሳስ 4/ 2011 ለፓስታና መከሮኒ ስንዴ ምርታቸው  ተገቢውን የገበያ ዋጋ በማጣት መቸገራቸውን  በባሌ ዞን  አጋርፋና ሲናና ወረዳዎች  አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ እንዳሉት  የፓስታና መከሮኒ የስንዴ ምርት ያዋጠናል ብለው ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም  እያመረቱት ላለው ምርት ተገቢው ዋጋ ማግኘት ባለመቻላቸው ተቸግረዋል፡፡ ከአርሶ አደሮቹ መካከል የአጋርፋ ወረዳ ነዋሪው አቶ ሙስጠፋ በከር እንዳተናገሩት በፓስታና መከሮኒ ስንዴ በመሳተፍ የቆየ ልምድ ቢኖራቸውም በገበያ እጦት የተነሳ የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ "ለፓስታና መካሮኒ ምርት  የሚውለውን ስንዴ ከተለመደው የስንዴ ሰብል ጋር እኩል በሚባል ዋጋ እየሸጥን በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል እልባት ሊሰጠን ይገባል " ብለዋል፡፡ የተለመደው የሰንዴ ሰብል በኩንታል እስከ 1ሺህ ብር እንደሚሸጥ ጠቁመው  ለፓስታና መካሮኒ ምርት  የሚሆነው ግን ከተለመደው በእጥፍ ብልጫ ያለው ዋጋ ያወጣልናል ብለው እንዳልተሳካላቸው አመልክተዋል፡፡ ሌላው የወረዳው አርሶ አደር አብዱላሂ ቃሲም በበኩላቸው የተለያዩ የግብርና ግብአትና አሰራሮችን በመጠቀም የሚያመርቱት የፓስታና መከሮኒ ስንዴ ከቀድሞ ከሁለት እጥፍ በላይ  በማምረት እስከ 65 ኩንታል  በሄክታር ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉት የሚያመርቱትን ምርት ራሳቸው ቀጥታ ለፋብሪካ በማቅረብ መሸጥ ስለማይችሉ ልፋታቸውን ደላሎች  እየተጠቀሙበት  ተቸግረዋል፡፡ በሲናና ወረዳ ሰልቃ ቀበሌ አርሶ አደር መሐመድ አብደላም  በሰጡት አስተያየትም ችግራቸውን በተመሳሳይ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው  የመኸር ወቅት ከሌሎች የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በ10 ሄክታር መሬት ላይ ላመረቱት የፓስታና መከሮኒ ስንዴ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽሀፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዳውድ አብዱሪ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ አርሶ አደሩ ከገበያ ጋር ተያይዞ ያነሱት ቅሬታ አግባቢነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት በአካባቢው የሚገኙ የገበሬዎች የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒዬኖች ምርቱን ከአርሶ አደሩ በመግዛት ለፋብሪካዎች እንዲያቀርቡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በተለይ አርሶ አደሩ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሳባቸውን የፓስታና መከሮኒ ስንዴ ምርት የገበያ ችግር እልባት ለመሰጠት በቅርቡ በሀገር ውስጥ ስንዴውን በግብዓትነት ከሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ጋር ስምምነት መፈረሙንም ጠቁመዋል፡፡ አቶ ዳውድ እንዳሉት  በቅርቡ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የምግብ ፋብሪካዎች ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረትአርሶ አደር ቀጥታ ለፋብሪካው ማቅረብ የሚችልበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ የተደራጀ  አቅም በመፍጠርም ባለፈው የመኸር ወቅት በዞኑ ስምንት ወረዳዎች ውስጥ ከ32ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት የፓስታና መከሮኒ ስንዴ በኩታ ገጠም ማልማቱን ጠቅሰዋል፡፡ በባሌ ዞን በ2010 /2011 የምርት ወቅት  የፓስታና መከሮኒ ስንዴ ጨምሮ በልዩ ልዩ የሰብል ዘር ከለማው 382ሺህ ሄክታር  መሬት 11 ሚሊዮን 500ሺህ  ኩንታል እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም