በሰብዓዊ መብት ጥሰት በተጠረጠሩ 33 ሰዎች ላይ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

67
አዲስ አበባ ታህሳስ 4/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ ሀጎስ አጽብሃ መዝገብ በሰብዓዊ መብት ጥሰት በተጠረጠሩ 33 ሰዎች ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ። ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ሲታይ በነበረው መዝገብ ፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ፣ የተጎጂዎችን ቃል ለመቀበል፣ የህክምና ማስረጃዎችን ለማሰባሰብና በወንጀሉ ክብደትና ውስብስብነት የ14 ቀን የምርምራ ጊዜ ጠይቆ ነበር። መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ የቀጠረው ችሎቱ የግራ ቀኙን አድምጦ ከታህሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የሚታሰብ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን ድርጊት ለይቶ የምርመራ ውጤት እንዲያቀርብ ለታህሳስ 16 ቀን 2011 ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል። መገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቡትን ዘጋቢ ፊልም በተመለከተ የትኛውና መቼ የሚለው ተለይቶ ስላልቀረበ ትዕዛዝ አይሰጥም፣ ቅሬታ ካለ በማንኛውም ቀን ፍርድ ቤቱ ጽህፈት ቤት ማቅረብ ይቻላል ብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም