በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሁኔታን የመፍጠር ትልቁ ድርሻ የራሳቸው የተማሪዎቹ ነው ተባለ

61
አዲስ አበባ  ታህሳስ 4/2011 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሁኔታን የመፍጠር ትልቁ ድርሻ የራሳቸው የተማሪዎቹ ሊሆን እንደሚገባ የጂንካ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብሬ ያንቲሶ ተናገሩ። በዘንደሮው የትምህርት ዘመን የጂንካ ዩኒቨርስቲን ለሚቀላቀሉ 1 ሺህ 500 ተማሪዎች ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ደማቅ አቀባበል አየተደረገ ነው። በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ በደቡብ ክልል የጂንካ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል። የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብሬ ያንቲሶ እንዳሉት የዩኒቨርስቲውን ሰላማዊ የመማረ ማሰተማር ሂደት ለማጠናከር የፀጥታ አካላት፣ የአካባቢው ማህበረሰብ እና ዩኒቨርስቲው የየራሳቸው ኃላፊነትና ሚና አላቸው። "ሆኖም በተለይ ግጭትን ቀድሞ በመከላከል ረገድ ትልቁን ድርሻ መያዝ ያለበት ራሱ ተማሪው ነው" ሲሉ ፕሮፌሰሩ አስገንዝበዋል። "ተማሪዎች ከቤታቸው የወጡበትን ዓላማ መዘንጋት የለባቸውም" የሚሉት ፕሮፌሰሩ ተማሪዎቹ ቅሬታ ሲገጥማቸው ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ የሚፈታበትን መንገድ ማሰብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። በትምህርት ተቋማት ውስጥ ከማንኛውም የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና መሰል እንቅስቃሴዎች በመታቀብና የግጭት አዝማሚያዎችን ቀድሞ በመጠቆም ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባ ነው ፕሮፌሰሩ የመከሩት። ከዚህ በፊት ዩኒቨርስቲው ከማህበረሰቡና ከዞኑ ጋር በፈጠረው ጠንካራ የቅርብ ግንኙነት የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ምንም ዓይነት ችግር ሳይከሰት የትምህርት ሂደቱ በተሳካ መንገድ መቀጠሉን አንስተዋል። በተማሪዎቹና በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር እንዲቻል ተማሪዎች በወር አንድ ጊዜ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡበት መርሃ ግብር ይቀረፃል ሲሉም ገልፀዋል። የማህበረሰብ አገልግሎቱ የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል የሚያስችል ትምህርትንና ማማከርን ጨምሮ የማህበረሰቡን አኗኗር በሚለውጡ የተለያዩ ተግባራት ላይ የሚያተኩር እንዲሆን ይደረጋልም ብለዋል። የጂንካ ዩኒቨርስቲና የአካባቢው ማህበረሰብ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ከ1 ሺህ 212 በላይ ለሚሆኑ አዲሰ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል አደርገዋል። በኢትዮጵያ አንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው። ትናንት በዚሁ ጉዳይ ላይ በተካሄደ ውይይት ላይ እንደተገለፀው የተማሪዎች የምዘና ስርዓት ከቦታ ቦታ መለያየት፣ የፈጣን ምላሽ እጦት፣ በግቢዎች ውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መኖር፣ የተማሪዎች አመዳደብ ስብጥር አለመኖር በዩኒቨርሲቲዎች ከሚታዩ ግጭት አባባሽ ሁኔታዎች መካከል ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም