የቡራዩ ከተማን የመሰረተ ልማት ችግር ለመፍታት የባለኃብቶች ድጋፍ ተጠየቀ

47
አዲስ አበባ ታህሳስ 4/4/2011 በኦሮሚያ ክልል ቡራዩ ከተማን የመሰረተ ልማት ችግር ለመፍታት ባለኃብቶች የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ። የከተማዋ  ባለኃብቶች ወደ አራት ሚሊዮን  የሚጠጋ  ብር  ድጋፍ ለማድርግ ቃል ገብተዋል። በከተማዋ  የሚታየውን የመሰረተ ልማት ችግር ከመንግሰት ጋር በመተባበር መፍታት በሚቻልበት መንገድ ላይ የከተማ አስተዳደሩና ባለኃብቶቹ ዛሬ ውይይት አድርጓል። በከተማው የውሃ፣ የመብራት፣ የመንገድ፣ የትምህርት እና የጤና አገልግሎት ችግሮች በስፋት እንደሚታዩ በውይይቱ ላይ ተገልጿል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በመንግስት በጀት የተለያዩ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አኳያ ሁሉንም ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ መፍታት የማይቻል በመሆኑ የባለኃብቶች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የከተማው ከንቲባ አቶ ሰለሞን ፈዬ ተናግረዋል። በዚህ ዓመት 36 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የውስጥ ለውሰጥ የጠጠር መንገድ ለመገንባት የባለኃብቶችንና የህበረተሰቡን ድጋፍ እንደሚሻ ነው ከንቲባው የገለፁት። በተለያየ  ምክንያት ሲጓተት የቆየው የሳንሱሲ- ኬላ አስፋልት መንገድ ግንባታን በዚህ ዓመት ለማስጨረስ ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል። ባለኃብቶች ከሚሰሩት የኢንቨስትመንት ስራ እና ከሚፈጥሩት የስራ ዕድል በተጨማሪ የተለያዩ የማህበረሰብ ተሳፎ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለግንባታ የሚያገለግሉ የተለያዩ ማሽነሪዎችን በግንባታ ወቅት ለመስጠት እና ባላቸው እውቀት ለመሳተፍም ቃል ገብተዋል። በከተማ አስተዳደሩ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታም ጠይቀዋል። ካንቲባው በበኩላቸው በሚቀጥለው ወር የባለሀብቶች እና ከተማዋን  አስተዳደር  ያካተተ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ጠቅሰው ይህም ያለውን ችግሮች በዘላቂነት ይፈታል ብለዋል። ባለኃብቶቹ በተለያየ ጊዜ 41 ሚሊዮን ብር የልማት ድጋፍ ለከተማዋ አስተዳደሩ ማበርከታቸውም ተጠቅሷል።  የከተማዋ ከንቲባም ባለኃብቶች ከዚህም በፊት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋ። በቡራዮ ከተማ  ከ8 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መዋእለ ንዋይ ያስመዘገቡ ከ478 በላይ ባለኃብቶች ያሉ ሲሆን ከ28 ሺህ ለሚልቅ ዜጋም የሥራ አድል ፈጥረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም