አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ዜጎች ከአፍ መፍቻና የስራ ቋንቋ በተጨማሪ ሁለት አገር በቀል ቋንቋዎችን እንዲማሩ እድል ይፈጥራል ተባለ

71
አዲስ አበባ ታህሳስ  4/2011 አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ሲሆን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከአፍ መፍቻና ከአገሪቷ የስራ ቋንቋ ውጪ ሁለት አገርበቀል ቋንቋዎችን የመማር ዕድል  እንደሚሰጠጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ይህም በኢትዮጵያ አገራዊ መግባባትን ለማጠናከርና ህዝቦችን ለማቀራረብ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሏል። የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ የፍኖተ ካርታውን የዝግጅት ሂደት አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ በፍኖተ ካርታው ላይ በመላው አገሪቱ በተለያየ ደረጃ ውይይቶች ተካሂደዋል። በዚህም ከ700ሺ በላይ የአጠቃላይ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት መምህራን  ውይይት ማድረጋቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ፍኖተ ካርታው አገሪቷ ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት በአጠቃላይ ትምህርቱ፣ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ዘረፎችን ለማሻሻል ያስችላሉ የተባሉ የተለያዩ አዳዲስ ጉዳዮች ይዟል። ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት መጀመሪያ ዕድሜ፣ ቋንቋ፣ የትምህርት ማጠናቀቂያ ጊዜ፣ የዩኒቨርስቲ ቆይታና የመምህራን ስልጠናን የተመለከቱ  ይገኙበታል። በዚህ መሰረት በፍኖተ ካርታው ጥናት ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከአፍ መፍቻና ከስራ ቋንቋ በተጨማሪ ሁለት ሌሎቸ አገር በቀል ቋንቋዎችን የሚማርበት ዕድል ይመቻቻል ነው ያሉት ሚኒስትሩ። ይህን ለመወሰን ቋንቋው እንዴት ይመረጣል፣ ማን ይመርጠዋል፣ የትኛው ክፍል ላይ ይጀመራል፤ የሚሉና የመሳሰሉትን መሰረታዊ ጉዳዮች ወደፊት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ይወሰናል ተብሏል። በፍኖተ ካርታው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት - መጀመሪያ ዕድሜ ስድስት ዓመት መሆን እንዳለበት የተቀመጠ ሲሆን እስካሁን በተደረገ ውይይት አሁን ባለው ሁኔታ ዕድሜው 7 ዓመት መሆን አለበት የሚል ሀሳብ መምጣቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም